የሦስታኛ አመት 34ኛ እሁድ (C OT-34) ክርስቶስ ንጉሥ

የሦስታኛ አመት 34ኛ እሁድ (C OT-34) ክርስቶስ ንጉሥ

ወንገል፥ ሉቃስ 23፥35-43

የዚህ እሁድ ንባብ የመዳን መርህ የሆነውን የኢየሱስን ንግሥና ይገልጽልናል። ኢየሱስ ንጉሥ ከመስቀል አናት ሆኖ በምን ዓይነት ሁኔታ ሊያድነን እንድሚችል እንረዳለን። እሱ የሚያገለግል ንጉሥ ነው፤ ያለው ስልጣን እስከ ሞት መውደድ ብቻ ነው።

በመስቀል ላይ፣ ኢየሱስ መንግሥቱን ይፈጽማል፣ እሱ ንጉስ ነው። ድሃ፣ የተራበ፣ የሚያለቅስ፣ የተጠላ፣ የተሰደደ፣ የተሰደበና ተቀባይነት ያላገኘ፣ ጠላቶቹን የሚወድና የሚባርካቸው፣ ክፉን በመሸከም ክፉን የሚያሸንፍ ነው።

ቁ35 “ሕዝቡ ቆሞ ይመለከት ነበር”፥ …

ስለስቅለቱ ማሰላሰል የአዲሱ ጥበብ መርህ ነው። በጎልጎታ ላይ የፊቱ መጋረጃ ስለሚነሳ ክርስቶስን ልንመለከተው እንችላለን፥ እርሱ ገደብ የሌለው ፍቅር ነው።

ቁ36 “ሆምጣጤ ሰጡት”፥ …

“በምግቤ ውስጥ ሐሞት ቀላቀሉ” (መዝሙር 69፥21)። ጥማቱ የሕይወትን ውሃ እንዲሰጠን ነው። እኛ ደግሞ በምላሹ ሞታችንን እንሰጠዋለን።

ቁ38 “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው”፥ …

ጲላጦስ “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው” በመጻፍ የፍርዱ ምክንያት መግለጽ ፍለጎ ነበረ (ማርቆስ 15፥26፤ ማቴዎስ 27፥37)። ወንጌላዊው ሉቃስ ግን ጽሑፉን የመስቀሉን ምስጢር መግለጫ አድርጎታል። በእውነት መስቀል በሁሉም ላይ ይነግሳል። የእርሱ ግዛት ግን ፍቅር ነው፥ “እኔም ከምድር ወደላይ ከፍ በተደረግሁ ጊዜ ሰውን ሁሉ ወደኔ እስባለሁ” (ዮሐ 12፥32)።

ቁ40 “እግዚአብሔርን አትፈራምን?”፥ …

የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው (መዝ 111፥10)። የተሰቀለው ክርስቶስ ደግሞ የአዲሱ ጥበብ መጀመሪያ ነው። አዳም በመታለልና በፍራቻ የሸሸበትን እውነተኛውን የእግዚአብሔር ፊት እንድናውቅ ያደርገናል።

ቁ42 “ኢየሱስ”፥ …

በሉቃስ ወንገል ያለ ተጨማሪ መግለጫ ኢየሱስን በስሙ የሚጠራው ይህ ሰው ብቻ ነው (17፥13፤ 18፥38.39)። ከኃጢያትና ከሞት በላይ ፍቅር ያለውን ጓደኛ አገኝቶአል።

“አስታውሰኝ”፥ …

ከዮሴፍ ጋር በእስር ቤት የነበረ ሰው ዮሴፍን ተመሳሳይ ንግግር ተናግሮ ነበረ (ዘፍጥረት 40፥13…      )። ይህ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ የሚገኝ ጥያቄ ነው። ሰው እንዳይረሳ ይፈራል። እግዚአብሔር ግን ፈጹም ሊረሳው አይችልም፥ “ሴት የምታጠባውን ልጅዋን ልትረሳ ትችላለችን? ወይስ ለወለደችው ልጅ አትራራምን? እርስዋ ትረሳ ይሆናል፥ እኔ ግን አልረሳችሁም” (ኢሳ 49፥15)። የተሰቀለው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ በአባቱ ዘንድ የጠፉት ልጆች ሁሉ መታሰቢያ ነው። ከእንግዲህ ወዲህ ማንም ሰው  እንደተተወና የተረገመ ሆኖ እንዳይሰማው ኢየሱስ ራሱን ከሁሉም በታች አደረገ።

“አስታውሰኝ”፥ …

ሞት አፋፍ ላይ ያለው ሰው የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት ሞት አፋፍ ላይ ያለውን ሰው ይጠይቃል፤ ድሃ ሰው መንግሥትን ለማግኘት ንብረት የሌለውን ሰው ይጠይቃል፤ በሞት በር ላይ ያለው ሌባ እንደ ሌባ ሞቶ መንግሥተ ሰማይን ይሰርቃል።  (Fulton Sheen)

ንስሐ ገባ፣ ያዳነውን ወደደ፣ የተሰማውን ሥቃይ እንደ መሥዋዕት አድርጎ ተቀበለ። በአንድ ቃል የክርስቶስን ልብ ሰርቆ የገነት በሮች ተከፍተወለታል።

ቁ43 “ከእኔ ጋር”፥ …

አንተ ከእኔ ጋር ትሆናለህ ምክንያቱም እኔ አማኑኤል ከአንተ ጋር እሆናለሁ። ከእኔ ጋር አልነበርክም፣ ሩቅ ሸሽተህ ነበረ። እኔ ደግሞ አንተ ከእኔ ጋር መሆን እንድትችል እስከ መስቀል ድረስ ተጓዝኩ።

“በገነት” …

እኔ ሕይወትህ ነኝና ይህ ራሱ መንግሥተ ሰማይ ነው።፡ ከእኔ ጋር ወደ መንግሥቴ እንድትመለስ ካንተ ጋር በመስቀል ላይ መጣሁ። ከአንተ ፈጹም አልርቅም፤ ከእንግዲህ ወዲህ አንተም ከእኔ አትርቅም። ለዘላለም አብረን እንኖራለን።

“ሕይወት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብሮ መኖር ነው፤ ጌታም ባለበት መንግሥቱም እዚያ ነው”

1ኛ ንባብ 2ኛ ሳሙኤል 5፥1-3

አጭር ትምህርት

ዛሬ ቤተክርስቲያን የሁሉ ነገር ንጉስ የኢየሱስ ክርስቶስን ክብረበዓል ታከብራለች።

1 “የዓለም ነገሥታት” እና “የዓለም ባለስልጣናት”

– እስካሁን ድረስ የአለም ባለስልጣናት ወደ አንድ ነገር ወይም ወደ አንድ ክልል ተሰራጭተው ነበር።

– ዛሬ ግን በኢኮኖሚና በፋይናንስ ግሎባላይዜሽን አማካይነት ከክልሎች ድምበር መሻገር ይሚችሉ የገንዘብና የኢኮኖሚ ኃይላት ተነስተዋል። ከስልጣናቸው የሚያመልጥ ነገር ስላለ ግን፣ እነዚህ ኃይላት የአለም ነገሥታትና ባለስልጣናት ናቸው እንጂ የሁሉ ነገር ነገሥታት መሆን አይችሉም።

– የገቢያቸውንና የገንዘብ አቅማቸውን ለማሳደግ፣ እነዚህ ባለስልጣናት በሰፊው በሰው አእምሮና ነፍስ ላይ ተጨማሪ ኃይል ማግኘት ችሎአል። በሰዎች አመለካከት፣ አመራረጥና አኗኗር ላይ አንድ አይነት አስተሳሰብ አስተጋብተዋል።

– እነዚህ አለምን የገዙ ባለስልጣናት ግን (ሰይጣን – “የዚህ ዓለም ገዢ” ዮሐ 12፥31 – ኃይልን የሚሰጣቸው ሲሆን በመካከላቸው እውነተኛ የዲያብሎስ ተከታዮች እንዳሉ እናውቃለን) የአለም ነገሥታት ሊሆኑ ይችላሉ እንጂ የሁሉ ነገር ንጉስ መሆን አይችሉም፣ ምክንያቱም ይህን መሆን የሚችል ክርስቶስ ብቻ ነው። የአለም ገዢዎች ዋናው የሚያስፈልግ ቁም ነገር ከእጃቸው ስለሚያመልጥ ይህን ቁም ነገር ለማስወገድ የማይሞክሩት ጥረት የለም።

2 “የሁሉ ነገር ንጉስ”

እነዚህ የዓለም ገዢዎች የፍጥረት ስልጣን የላቸውም፣ የሰውን ልጅ ከሥጋውና ከነፍሱ ሞት የማስነሳት ኃይል የላቸወም። ማጥፋት የሚችሉትን ግን ያጠፋሉ፥

– የሰውን ዘር ያጠፋሉ (ፅንስ ማስወረድ ወይም ንጹህ ሕይወት ማጥፋት፣ ሕፃናት መግደል፣ ያረጁትንና የታመሙትን ማስወገድ፣ አእምሮዎች መቆጣጠር)።

– ካስተሳሰባቸው ጋር የማይሰማማ ከማህበር ማሳደድና ማግለል።

– በመጀመሪያው እግዚአብሔርን ከሰው ሕይወት አስወግደዋል፣ ከዚያ በኋላ እግዚአብሔርን ተክተው አዲስ የሰውን ዘር ሕብረት ገንብተዋል (new humanism)። ቀጥሎም ሁሉም ሃይማኖት ተመሳሳይ በማድረግ ማንነት የሌለው ሃይማኖት ለመፍጠር ይፈልጋሉ (religious relativism)።

– ቤተክርስቲያን ውስጥ የ “ዓለም ገዢዎች” ባሪያ የሚሆኑ አካላት የሁሉ ነገር ንጉስ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚክዱ ናቸው። በትንሳኤው አማካኝነት ከኃጢያትና ከሞት ሰውን “የጠገነ” ክርስቶስ ብቻ ነው። “የዓለም ገዢዎች”፣ “የዚህ ዓለም ገዢ” ይህን ማድረግ አይችሉም፣ እንዴት እንደሚደረግም አያውቁም፣ ምክንያቱም በቂ ኃይል የላቸውም። በዚህም ምክንያት ያለ ክርስቶስ መገንባት ይቻላል በማለት ሰለባዎቻቸውን ያታልላሉ። ግን አይሰራም! በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ሠርቶ አያውቅም፣ ወደፊትም በጭራሽ አይሰራም! ሰላምና ብልጽግና፣ ፍትሕና እድገት በክርስቶስ ብቻ መሆኑ የዛሬው ክብረ በዓል ያስተምረናል። እያንዳንዳችን በመስቀል ላይ ከሚገኙት ከሁለቱ ሌቦች መካከል ማን መሆን እንደምንፈልግ መውሰን አለብን።

Leave a reply