የሰብከተገና 4ኛ እሁድ (A ADV-4)

የሰብከተገና 4ኛ እሁድ (A ADV-4)

ወንገል፥ ማቴዎስ 1፥18-24

ቁ18 “ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ሁኔታ እንዲህ ነው፥ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ እያለች፣ ሳይገናኙ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች”፥ …

“ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ሁኔታ”፥ … እግዚአብሔር በሰው ሊፈጠር አይችልም፥ ሰው ግን ሊቀበለው ይችላል። “ዮሴፍ” በዕብራይስ ማለት “እግዚአብሔር ይጨምር” ማለት ነው። እግዚአብሔር ትሑት የጽዮን ልጅ በሆነች በማርያም አማካይነት “በጨመረ” ልደት ስላመነ፣ ዮሴፍ ወደ እግዚአብሔር ልጅ ትውልድ ሐረግ ገብቶአል። ዮሴፍ ለራሱ ስለማይበቃ (Pascal) እራሱን ለታላቅ ምስጥር ክፍት የሚያደርግ ሰው ሁሉ አምሳል ነው።

“እናቱ ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ ሳለች”፥ … የሙሴ ሕግ ባዘዘው መሠረት፣ ከእጮኝነት ዝግጅት እስከ ሠርግ አንድ ዓመት ያልፍ ነበር። በመደበኛ ሠርግ ቀን ሙሽራይቱ ወደ ሙሽራ ቤት ትወሰድ ነበር። ሆኖም እጮኝነትና ጋብቻ በሕብረተሰብ ፊት ተመሳሳይ ናቸው።

እንደ ዮሴፍ ሁሉ ሰው የክርስቶስን እናት እጮኛ አድርጎ እንዲኖር ይጋበዛል። ለእሷ “እሺ” ሲል ለእግዚአብሔር ስጦታ “እሺ” ይላል።

ማርያም የመጀመሪያ አማኝ ናት፥ በእሷም አማካይነት ቃል ሥጋ ሆነ። እሷን የሚያገባ በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና በአብ ሥራ በውስጧ የተፀነሰውን ልጅም ያገኛል። ማርያምና እስራኤል ወደወልድ የሚያመራ መደበኛ መንገድ ናቸው፥ የጌታችን ሥጋና ለእያንዳንዱ ሥጋ ለባሽ ራሱን የሚሰጥ ጌታ የሚገኘው በማርያምና በእውነተኛ እስራኤል አማካይነት ብቻ ነው።

ከላይ እንደተባለው “ዮሴፍ” ማለት “እግዚአብሔር ይጨምር!” ማለት ነው። “ዮሴፍ” ሟች ሆኖ ዘላለማዊን የማይሞት የሚመኝ ሰው ሁሉ ምስጢራዊ ስም ነው። ከዚህ አለም ይሚሻገር ብቻ ነው ሊሞላው የሚችል። ሰው የተፈጠረው ለዚህ መለኮታዊ “መጨመር” ነው፥ “ጌታ ሆይ፣ የራስህ ፍጡራን ነንና በአንተ እስከምናርፍ ድረስ ልባችን ዕረፍት አያገኝም” (AUGUSTINE)

ቁ19 “እጮኛዋ ዮሴፍ ደግ ሰው ስለነበረ፣ ማርያምን በሰው ፊት ሊያጋልጣት አልፈለገም፤ ስለዚህ በስውር ሊተዋት አሰበ”፥ …

“በስውር ሊተዋት አሰበ” … ዮሴፍ ማርያምን ሊተዋት ያሰበ ሊያከብራት ነው እንጂ ተጠራጥሮ አይደለም።

ቁ20 “የጌታ መልአክ በሕልም ተገልጦለት እንዲህ አለው፥ የዳዊት ዘር ዮሴፍ ሆይ! እጮኛህ ማርያም የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ስለሆነ፣ እርስዋን ወደቤትህ ለመውሰድ አትፍራ”፥ …

“የጌታ መልአክ በሕልም ተገልጦለት”፥ … ሰው “ይበቃል” በሚልበት ጊዜ (1ነገሥት 19፥4…)፣ እግዚአብሔር ስጦታውን ይለግሳል (መዝሙር 127፥2)፥ ከወንድሙ የሚሸሸውን አባታችን ያዕቆብ በሕልም አናግሮአል (ዘፍጥረት 28፥10…)፤ ከነጉሥ የሚያመልጠውን ነቢይ እልያስ በሕልም ያገኛል (1ነገሥት 19፥1…)። በመጨረሻም እግዚአብሔር በልጁ እንቅልፍ አማካይነት (በመስቀል ላይ በመሞት) በሞት እንቅልፍ ላይ ያለውን እያንዳንዱ ሰው ያድናል፥ የአበ ቃል በሌሎች ቃላት እንቅልፍ ላይ ይናገራል፣ መላኩ በሰው ዝምታ ላይ ራሱን ይገልጣል።

“አትፍራ”፥ … “ፈራሁ”(ዘፍጥረት 3፥10) ለመጀመሪያ ጊዜ ሰው ለእግዚአብሔር የተናገረው ቃል ነው። “አትፍራ” ለሰው ራሱን ሲገልፅ እግዚአብሔር የሚናገረው የመጀመሪያው ቃል ነው።

“እርስዋን ወደቤትህ ለመውሰድ አትፍራ”፥ … ማርያም ለሰው ሁሉ የእግዚአብሔር ስጦታ አገናኝ ናት። እናትን የሚክድ ልጇንም ይክዳል። ታሪካዊ አገናኝ አያስፈልግም የሚል ግምት እስከ ዛሬ ያልጠፋ ጥንታዊ መናፍቅነት ነውና “docetism” ይባላል። ኢየሱስን ከማርያም፣ ከእስራኤል፣ ከቤተክርስቲያንና ከወንድሞች መለየት ማለት ሁሉን ሥጋ ለባሽ የሚያድነውን የኢየሱስን ሥጋ መካድ ማለት ነው። ክርስትና በሰው አእምሮ ብቻ የታቀደ ፍልስፍና ከሆነ፣  “ግኖሲስ” ይሆናል።

ቁ21 “እርስዋ ወንድ ልጅ ተወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ስለሚያድን ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ”፥ …

ማሪያም ትወልደዋለች፣ አንተ ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ፣ አንተ ዘመዱ ትሆንና እርሱ ዘመድህ ይሆናል። የሰው ታላቅ ክብር ለ“ስም” ስም መስጠት ነው፣ እንደወዳጅ ከርሱ ጋር መነጋገር ማለት ነው።

ቁ23 “እንሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙም ዐማኑኤል ተብሎ ይጠራል። ዐማኑኤል ማለትም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው ማለት ነው”፥ …

ኢየሱስ “የሚያድን” “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” ስለሆነ ነው። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ደግሞ ማን ሊቃወመን ይችላል? (ሮም 8፥32…)። “ከእኛ ጋር” ማለት ግንኙነት፣ ቅርበት፣ አንድነት፣ መጽናናት፣ ደስታ፣ ጥንካሬና ልውውጥ ማለት ነው። እኛም ሁልጊዜ ከኢየሱስ ጋር እስከምንሆን ድረስ  (1ተሰ 4፥17) እርሱ ሁል ጊዜም ከእኛ ጋር ነው (28፥20)።

ቁ24 “ዮሴፍ ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ የጌታ መልአክ ባዘዘው መሰረት እጮኛውን ማርያምን ወደ ቤቱ ወሰዳት”፥ …

እግዚአብሔር ስለገለጸለት ቃል፣ የዮሴፍ እንቅልፍ አዲስ ሂወትና ትንሣኤ ይሆናል። ዮሴፍ ቃሉን “ሰምቶ ያደርጋል”፥ ለእግዚአብሔር የሚታዘዝ አዲስ አዳም ነው። ከጥንት የውሸት ቅዠት ነቅቶ፣ በዓይኖቹ ፊት ሙሽራይቱንና ከርሷ ጋር ሕይወት ሰጭ የእግዚአብሔርን ልጅ ያገኛል።

1ኛ ንባብ፥ ኢሳይያስ 7፥10-14

ቁ14 “እንግዲህ እግዚአብሔር ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እንሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም ዐማኑኤል ብላ ትጠራዋለች”፥ …

“ዝም ብሎ “እንሆ ድንግል ትፀንሳለች” አይልም። በመጀመሪያ “እነሆ፣ እግዚአብሔር ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል” ይላል። ከዚያም በኋላ “እንሆ ድንግል ትፀንሳለች” ብሎ ይጨምራል። መውለድ ያለባት ሴት ድንግል ካልሆነችና የምትፀንሰው በተለመደ ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ከሆነ፣ ይህ ምን ዓይነት ምልክት ይሆናል? ምልክቱ ያልተለመደና ልዩ መሆን አለበት፣ አለባለዚያ እንዴት ምልክት ሊሆን ይችላል?” (JOHN CHRYSOSTOM)

“የሚሰጥ ምልክት የእፃን ልደት ብቻ አይደለም፥ የድንግል አስደናቂ መፅነስም ምልክት ነው። ይህ አስደናቂ መፅነስ የልጁን እናት ወሳኝ ሚና የሚያመለክተው በትልቅ ተስፋ የተሞላ ክስተት ነው” (SAINT JOHN PAUL II)

Leave a reply