የሦስታኛ አመት 31ኛ እሁድ (C OT-31)

የሦስታኛ አመት 31ኛ እሁድ (C OT-31)

ወንገል፥ ሉቃስ 19፥1-10

ቁ1 “ኢየሱስ ወደ ኢያሪኮም ከተማ ገብቶ ያልፍ ነበር”፥ …

ቀደም ባለው ምዕራፍ (ሉቃስ 18) ኢየሱስ ወደ ኢያሪኮ ቀርቦ ዓይነሰውሩን ፈውሷል። አሁን ገብቶ ከተማውን እንደ አሸናፊ ሆኖ ያቋርጣታል። ሊደፈር የማይችል የኢያሪኮ ምሽግ ፈርሶአል። ዐይን ተፈወሰ፣ ብርሃንም ወደ ልብ የሚገባ ሲሆን ድንዛዜውን ይቀልጣል። የሰው ጨለማ ተቀደደ።

ቁ2-4 “እነሆም ዘኬዎስ የሚባል ሰው፥ እርሱም የቀራጮች አለቃ ነበረ፥ ባለ ጠጋም ነበረ። ኢየሱስንም የትኛው እንደ ሆነ ሊያይ ይፈልግ ነበር፤ ነገር ግን ቁመቱ አጭር በመሆኑ ከሕዝብ ብዛት የተነሳ አቃተው። ኢየሱስ በዚያ በኩል ያልፍ ስለነበር ዘከወዎስ ያየው ዘንድ ወደ ፊት በመሮጥ በአንድ ሾላ ዛፍ ላይ ወጣ”፥ …

ሰዎቹ መንገድ ውስጥ ስለገቡ ኢየሱስ እንዳይታይ ዘኬዎስን ከልክለውት ነበር። ዘኬዎስ ግን ሕዝቡን ችላ በማለት “ሞኝ ፍሬ” የሚያፈራ የሾላ ዛፍ ላይ ወጣ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው፥ “እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው” (1ኛ ቆሮ 1፥23)። የአለም ምሁራን “የተሰቀለውን አምላክ የሚያመልኩ ምን ዓይነት አእምሮ አላቸው?” በማለት ስለ ክርስቶስ መስቀል ይስቁብናል … አዕምሯችንን ሞኝ ይሉታል፤ የፈለጉትን ይበሉ፣ በእኛ በኩል ግን፣ ወደ ሾላ ዛፍ ላይ ወጥተን ኢየሱስን እንይ። ዘኬዎስ ሾላ ዛፍ ላይ ይዉጣ፣ ትሑት ሰውም መስቀል ላይ ይውጣ። ዛፉን መወጣት ብቻ በቂ ነው። ስለ ክርስቶስ መስቀል ማፈር የለብንም (AUGUSTINE)

ቁ4 “በአንድ ሾላ ዛፍ ላይ ወጣ”፥ …

ዘኬዎስ ዛፉ ላይ እንደሚወጣ ኢየሱስም ሁሉን ሰው በሚያቅፈው ዛፍ በመስቀል ላይ ከፍ ለማለት ወደ ኢየሩሳሌም ይወጣል። ዛፉ የድህነትና የከፍተኛ ትህትና ዛፍ ነው። ከዚህ ዛፍ – እውነተኛ የሕይወት ዛፍ – ዘኬዎስ የመምህሩን ቸርነት ያውቃል። ጌታውን ያያል። ሊደፈር የማይችል የያሪኮ ምሽግ ፈርሶአል። ዐይን ተፈውሶ መሲህን ያያል።

ቁ5 “ኢየሱስም ወደዚያ ስፍራ በደረሰ ጊዜ፥ አሻቅቦ አየና። ዘኬዎስ ሆይ፥ ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ አለው”፥ …

የመምጣቱ ምክንያት በእኛ ውስጥና ከእኛ ጋር ለመኖር ነው። እንዲያውም ከእኛ ጋር የሚኖር እግዚአብሔር አማኑኤል ነው።

ቁ10 “የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና አለው”፥ …

መላው መጽሐፍ ቅዱስ  እግዚአብሔር የሚያደርገውን የሰው ፍለጋ ይነግረናል። በፍቅሩ ምክንያት፣ ሁሉንም ትቶ የጠፋውን ለመፈለግና ለማዳን ራሱን ዝቅ ያደርጋል። ነገር ግን ቀድመው እሱን የሚፈልጉትን ብቻ ሊያገኝ ይችላል።

1ኛ ንባብ ጥበብ 11፥22-12፥2

አጭር ትምህርት

1 ኢየሱስ የንግድ ከተማ የነበረውን ኢያሪኮ ተሻገረ። የመጨረሻውን የሕይወታችን አላማ ሳናስተናገድ አለማዊ ጉዳዮችና ጊዜአዊ ንግዶች ላይ ብቻ በማተኮር፣ በመንፈሳዊ እድገት እንደ ዘኬዎስ ቁመት አነስተኛ እንሆናለን፣ ወደ ሰማያዊ ነገሮች ከፍ ለማለት ያቅተናልና እንደሚበጠብጠው ሕዝብ ብዛት በንግድና በልዩ ጉዳዮች ብዛት እንጨናነቃለን። በዚህ መንፈሳዊ አነስተኝነት ኢየሱስን ማየት አይቻልም፥ ከምድራዊ ነገሮች ለመራቅ ጥረት በማድረግ ወደላይ መውጣት ያስፈልጋል።

2 ነገር ግን እሱን ከመፈለግህ በፊት ኢየሱስ ቀድሞ እንደፈለገህ ትገነዘባለህ። ኢየሱስን ማየት ከፈለግህ ወደላይ መውጣት ያስፈልጋል (ፈለጋ ከፍ በማለት)። እንዲያውም ዘኬዎስ በሾላ ዛፍ ላይ ይወጣል፣ ሁሉ ታስቦአል። በታሰበ ነገር ውስጥ ግን ያልታሰበ ነገር ይከሰታል፥ ዘኬዎስ ኢየሱስን ከማየቱ በፊት ኢየሱስ ዘኬዎስን አይቶታል። ምክንያቱም የኢየሱስ እውቀት መርህ ከራሳችን ጥረት ወይም ችሎታ ሳይሆን ከኢየሱስ ራሱ ይመነጫል። እግዚአብሔር ውስብስብ አይደለምና የተወሳሰበ ዘዴን በተጠቀምን ቁጥር አናገኘውም። ጥበብ የሚፈልጉትን ይስባል። እራሳችንን እንድንማረክ መፍቀድ አለብን። የእግዚአብሔር ፍለጋ እንዲፈጸምና እንዲደርሰን መፍቀድ አለብን። ፍለጋው የሚፈጸመው እሱን ስትፈልግ አንተን ካገኘህ ነው።

Leave a reply