የአንደኛ አመት 17ኛ እሁድ (A OT-17)

የአንደኛ አመት 17ኛ እሁድ (A OT-17)

ወንገል፥ ማቴዎስ 13፥44-52

√ መንግሥተ ሰማይ፣ የተሸሸገ ሀብትና እጅግ ክቡር የሆነ እንቁ አንድ አይነት ነገር ናቸው? የተሸሸገ ሀብትና እጅግ ክቡር የሆነ እንቁ ሁለቱም መንግሥተ ሰማይ ከሆኑ፣ በተሸሸገው ሀብትና እጅግ ክቡር በሆነው እንቁ መካከል ምን ልዩነት አለ? የተሸሸገ ሀብት እጅግ ዋጋ ያለው እንቁ ራሱ ሊሆን አይችልምን? ሁለቱም አንድ አይነት ነገር አይደሉምን?

> አላስፈላጊ ምሳሌዎችን አባዝቷል! ግን ኢየሱስ አላስፈላጊ ምሳሌዎችን ያባዛል ብለህ ታምናለህን? በዚህ ጉዳይ በጥንቃቄ ማንበብ ያለብን እኛ ነን እንጂ! “መንግሥተ ሰማይ እርሻ ውስጥ የተሸሸገውን ሀብት ትመስላለች…” (44)፤ “መንግሥተ ሰማይ ክቡር የሆነውን እንቁ ለመግዛት የሚፈልግ ነጋዴን ትመስላለች” (45)። አንድ አይነት ነገር እንዳልሆነ አስተውለሃል? መንግሥተ ሰማይ ክቡር የሆነው እንቁ አይደለችም፣ መንግሥተ ሰማይ ክቡር የሆነውን እንቁ ለመግዛት የሚፈልግ ነጋዴ ናት።

> የተሸሸገው ሀብትና ነጋዴው ምን አይነት ልዩነት አላቸው? የተገኘ ሀብት ድርጊትን ፈጻሚ ወይስ ድርጊትን ተቀባይ ነው? ድርጊትን ተቀባይ ነው (የተገኘ ነው)። ፈላጊው ነጋዴ ድርጊትን ፈጻሚ ወይስ ድርጊትን ተቀባይ ው? ድርጊትን ፈጻሚ ነው (ፈላጊ ነው)። የኢየሱስ ምሳሌ ሦስት ቃላትን ያካትታል (ሀብት፣ ነጋዴና ክቡር እንቁ) እንጂ የምሳሌው ቁልፍ ሀሳብ ሌላ ነው። የምሳሌው ዋና ሀሳብ፣ መንግሥተ ሰማይ በአንድ በኩል ድርጊትን ተቀባይ ሲሆን (የተገኘ ሀብት) በሌላ በኩል ደግሞ ድርጊትን ፈጻሚ ሆኖ እንደሚገለጽ ነው (ፈላጊ ነጋዴ)።

[ከዚህ በኋላ በእንግሊዝኛ ቃል ተጠቅሜ ድርጊትን ፈጻሚ “active” እና ድርጊትን ተቀባይ “passive” እለዋለሁ]

√ በዚህ active እና passive ውስጥ መወገድ ያለባቸው ሁለት ስህተቶች አሉ።

> መንግሥተ ሰማይ passive ሆኖ የሚገኝ ነገር ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ እኛ እርሱን ለማገኘት አቅም ይኖረን ነበር። [መንግሥተ ሰማይ አያግዝህም፥ “ከፈለከኝ ታገኘኛለህ፣ ካልፈለከኝ አታገኘኝም”። ኢየሱስ ጥሩ ምሳሌወ ይሰጣል፤ እሱን ለመምሰል መልካም ፈቃድ ካለህ ትድናለህ፣ መልካም ፈቃድ ከሌለህ ግን አትድንም][1] ይህ እውነት ይመስላል… ግን እውነት ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም መንግሥተ ሰማይ ኢየሱስ ከሆነና ኢየሱስ ደግሞ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ ከሆነ፣ ተራ ሰው በራሱ መልካም ፈቃድ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ የሆነውን መምሰል ይችላልን? በትክክል አይመስልም። ሥነ-መለኮታዊ ስህተት ነው። ተራ ሰው ሆኜ እንዴት ሰውና አምላክ የሆነውን መምሰል እችላለሁ? መንግሥተ ሰማይ passive ብቻ ሊሆን አይችልም (እኛactive ብቻ መሆን አንችልም)፣ ስለዚህ መንግሥተ ሰማይ በመልካም ፈቃዳችን የሚገኝ ብቻ ሊሆን አይችልም።

> በተቃራኒው ግን መንግሥተ ሰማይ ሙሉ በሙሉ active መሆኑንና እኛ ደግሞ ሙሉ በሙሉ passive መሆናችንን መግለጽ ትክክል አይደለም። [እግዚአብሔር ብቻ ሁሉን ይሠራል፣ እኛ ደግሞ ምንም አንሠራም። የእግዚአብሔር መንግሥት የእግዚአብሔር ጉዳይ ነው እንጂ የእኛ ጉዳይ አይደለም። እንዲሁም መንግሥተ ሰማይ ሊገባ የሚፈልግ እንደማይመረጥና ሊገባ የማይፈልግ እንደሚመረጥ ሊከሰት ይችላል][2] ይህ ሌላ ሥነ-መለኮታዊ ስህተት ነው

ይህ ቋጥሮ እንዴት ይፈታል? መንግሥተ ሰማይ ሁለቱም active (ፈላጊ ነጋዴ) እና passive ነው (የተገኘ ሀብት) በማለት ነው። እግዚአብሔር ያሳትፈናል፥ እግዚአብሔርን ከፈለግን እግዚአብሔር አስቀድሞ አሳትፎናል። እግዚአብሔር የአእምሮአችንና የልባችን ምርምር ማብቂያ በመሆኑ፣ እርሱ passive ነው፣ እኛ active ነን። እንደ ክቡር እንቁ በአይኑ ተወድደን እኛን በመፈለጉ፣ እግዚአብሔር active ነው፣ እኛ passive ነን።

√ መንግሥተ ሰማይ እጅግ ክቡር የሆነውን እንቁ ባገኘ ጊዜ ያለውን ሁሉ ሸጦ ያንን እንቁ የሚገዛውን ነጋዴ ትመስላለች (45-46)። ነጋዴው እግዚአብሔር ነው፣ እንቁ ሰው ነው። ሰውን ለማዳን እግዚአብሔር ልጁን አሳልፎ ሰጠ። “እግዚአብሔር አለምን እጅግ ስለወደደ አንድ ልጁን ሰጠ”(ዮሐንስ 3፥16)።

> ለምን የሰው ነፍስ በእግዚአብሔር የተወደደች እጅግ ክቡር እንቁ ናት? በተሸሸገ ሀብት፣ በእግዚአብሔር ስለምትሳብ ነው።

የተሸሸገ ሀብት የሚስብ ነገር ነው? አዎ ይስባል። ሀብት ስለሆነና ተሸሽጎ ስለሚገኝ ይስባል። ሀብት መገኘት ይፈልጋል፣ ከመገኘቱ በፊት ግን ይስብሃል። የሰማይ መንግሥት ውበት የሚስብህ ከሆነ እጅግ ክቡር እንቁ ትሆናለህ።

የሰማይ መንግሥት ከሳበህ፣ ከሰማይ መንግሥት ጋር ትመሳሰላለህ? አዎ ትመሳሰላለህ። ናፍታ መጠጣት ትችላለህን? አትችልም። ውሃና ጠጅ ትጠጣለህ፣ ናፍታ ግን አትጠጣም። መኪና ውስጥ ቢራ አይጨመርም፣ ምክንያቱም ቢራና መኪና አይመጣጠኑም።

አንድ ሰው በተሸሸገው ሀብት ውበት የሚሳብ ከሆነ፣ ከዚያ ሀብት ጋር የሚያዋሕደው ነገር አለው ማለት ነው። በእግዚአብሔርና በአንተ መካከል ተመሳሳይ የሚያደርጋችሁ ነገር አለ (እግዚአብሔር ይስብሃልና አንተ እግዚአብሔርን ትስባለህ)።

> ሰው እጅግ ክቡር እንቁ የሚሆን በሰማይ መንግሥት ተስቦ ወደርሱ ፍልጋ ስለሚወጣ ነው። በእርግጥ ግን፣ የሰማይ መንግሥት ራሱ አስቀድሞ እየሳበው በሰው መንገድ ገብቶ ይማርከዋል።

ወደዚህ አስተያየት ካልገባን፣ ወይም ሁሉን ነገር ራሳችን የምንሠራ፣ ወይም ሁሉን ነገር እግዚአብሔር የሚሠራ ይመስለናል። እግዚአብሔር አይሸነፍም፣ እግዚአብሔር እኛን የራሱ ያደርገናል እንጂ እኛ እርሱን የራሳችን አናደርገውም፣ ያሸንፋል እንጂ አይሸነፍም

ክቡር እንቁ ነን፣ ምክንያቱም ክቡር ነገር ይስበናል። የእግዚአብሔር ዘላለማዊና አድካሚ ፍለጋ ዓላማ ነን፣ ምክንያቱም የፍለጋችን ኣላማ የሆነው እግዚአብሔር ይስበናል።

[1] ይህ ሥነ-መለኮታዊ ስህተት pelagianism ይባላል

[2] predestination ይባላል

Leave a reply