ወንገል፥ ማቴዎስ 11፥25-30
1 “አባት ሆይ! … አመሰግንሃለሁ” (25)፥ … በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ወልድ ወልድ የሚሆንበት “አባባ” የሚል ቃል በልባችን ውስጥ ይመነጫል (“አባባ” ሕፃን ልጅ አፍ መፍታት በሚጀምርበት ጊዜ የሚናገረው ቃል ነው)። በአብና በወልድ መካከል ባለው መግለጽ በማይቻል ውይይት ውስጥ እንገባለን። በቅድስት ሥላሴ ውስጥ እንገባለን።
> ፍጥረት ሁሉ አላማውን ይፈጽማል፥ የእግዚአብሔር ልጅ እና የሰው ልጅ በሆነው በኢየሱስ ዋሽንት ድምጽ ተደስተን፣ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያዋሕደውን የሰርግ ግብዣ እንሳተፋለን። በስጋው አማካይነት እያንዳንዱ ስጋ ከክብር ጋር ይዋሐዳል።
> አባባ ተብሎ የሚጠራ “የሰማይና የምድር ጌታ ነው” (25)። ለእኛ ቅርብና አፍቃሪ የሆነ አባታችን ልዑልና ሁሉን የሚችል ነው። እንደ ጣዖት እንዳይታይ፣ እግዚአብሔር የሚገለጸው በተቃራኒ ቃላት አማካይነት ነው፥ እርሱ ቅርብና ልዑል፣ አፍቃሪና ኃያል፣ ትሁትና ታላቅ፣ እናትና አባት ነው።
> የአለም ጥበበኞችና ብልጦች ስልጣን ያለውን ጥበበኛ አምላክ እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። ትሁታንና ታናናሾች ግን የእግዚአብሔርን ጥበብና ኃይል የሚያገኙ በኢየሱስ ትህትና አማካኝነት ነው። ትንሽ ከሆንሽ ታዪዋለሽ፣ ትልቅ ከሆንሽ ግን ይደበቅብሻል።
√ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፥ ስጋው የፍጥረትና የፈጣሪ፣ የአባትና የልጆቹ መገናኛ በር ነው። ሰማይና ምድር የሚያገናኝ የእያዕቆብ መሰላል ነው (ዘፍጥረት 28፥10-17፤ ዮሐንስ 1፥51)። ቤተክርስቲያን በኢየሱስ አማካይነት የአብ ልጆች መሆናቸው በተገለጸላቸው ታናናሾች ላይ የተመሰረተች ናት።
2 “እናንተ ሁሉ … ወደ እኔ ኑ” (28)፥ … ኢየሱስ ከእርሱ ጋር ወደ አብ ፍቅር እንድንገባ ይጋብዘናል፣ ወደ ጥበብ ግብዣ ይጋብዘናል (ሲራክ 51፥23-27 “ያልተማራችሁ ሁሉ ኑ… እርሷ ነፍሳችሁን እየጠማች እስከ መቼ ያለ ጥበብ መሆን ትፈልጋላችሁ? … ያለ ገንዘብ ግዟት። አንገታችሁን ለቀንበሯ አቅረቡ… ቅርብ ናትና ትገኛለች… ብዙ ሳይደክመኝ ትልቅ ሰላም አገኘሁ”)። ኢየሱስ ራሱ ላልተማሩና ልምድ ለሌላቸው የሚቀርብ ጥበብ ነው፥ በነፃ የሚሰጥና ጣፋጭ ናት፣ በቀላል ትገኝና ትልቅ ሰላም ትሰጣለች። እውነተኛ ምግብ እግዚአብሔርን እንደ አባትና ራሳችንን እንደ ልጆች ማወቅ ነው፥ ይህ ደግሞ በአንድ አባት ልጆችና በወንድማሞች ፍቅር የሚያስደስት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው።
> በፍጥረትና በሰው ታሪክ ውስጥ፣ በሙሴ ሕግና በቃል ኪዳን አማካይነት እየተጋረደች የተገለጸች የማትታይ ጥበብ አሁን ተገለጸች። በኢየሱስ አማካይነት ቀርባ ትገኛለች፥ የአብና የወልድ ፍቅር ውጤት ናት።
√ ለሙሴ የተሰጠ ሕግ ለህይወት የሚጠቅም ሲሆን፣ ህይወትን ግን አይሰጥም። ከባድ ሽክም ነው፥ ያዛል፣ ይከሳል፣ ይፈርዳል… ፍቅር ግን “ሕግን ሁሉ ይፈጽማል” (ወደ ሮም 13፥10፤ ማቴዎስ 7)። አንድ እናት በፍቅር ለልጇ የምታደርገወን ሁሉ ማዘዝና ማስገደድ የሚችል ምንም ሕግ የለም።
> ፍቅር ሕግን አይቃወምም (ሕግን የሚቃወም ሁሉ ራሱ የሕግ ባርያ ነው)። በፍቅር የሚመራ ሁሉ ግን የሕግ ታዛዥ መሆኑን ትቶ የፍቅር ታዛዥ ይሆናል፥ ፍቅር ራሱ አዛዡና ሕጉ ይሆናል። የነፃነት ሕግ ነው።
ሕግ ካሁን በኋላ ደስታ፣ እረፍትና በሰንበት ቀን ለምግብ የሚጋብዝ አዲስ ህይወት ነው (12,1)፥ እንደ እግዚአብሔር መኖር ነው። እረፍትና የሰው እውነተኛ ቤት እግዚአብሔር ራሱ ነው (29)። ሰው በአብና በወልድ መካከል ባለው ፍቅር ውስጥ ቤቱን ሠርቷል።
> “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ” (29)፥ … ቀንበር የቤት እንስሳ በራሱ ኃይል ይበልጥ መጠቀም እንዲችል የሚያደርግ ማሠሪያ ነው። የኢየሱስ ቀንበር ልዝብ ነው። “በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው” ፍቅር እኖራለሁ (ወደ ገላትያ 2፥20)። “ወፍ ክንፎቹ ከተነቀሉበት፣ ክብደቱ የሚቀንስ ቢመስልም፣ መሬት ላይ ይታገዳል። ክንፎቹን ስጠው፣ ይበራል” (Augustine †430)። የፍቅር ሕግ የምንሸክመው ሽክም ሳይሆን፣ የሚሸከመን ሽክም ነው። የማይከብድ ክብደትና ቀላል የሚያደርገን ሽክም ነው። ፍቅር የውስጣችን መለኮታዊ ኃይልና የእግዚአብሔር መንፈስ ራሱ ነው።
> “ከእኔም ተማሩ” (29)፥ … “አለምን ለመፍጠር ከእኔ መማር አይጠየቅባችሁም፣ የሚታየውንና የማይታየውን ለመፍጠር፣ ተአምራትን ለመሥራትና የሞቱትን ከሞት ለማስነሳት አንድትማሩም አልጠይቃችሁም። ይልቁንም የዋህና ትሑት ስለሆንኩ እንደኔ የዋሃንና ትሁታን ሁኑ። ወደ ከፍተኛ ደረጃ መድረስ ከፈለጋችሁ፣ ከዝክትኛ ደረጃ ጀምሩ። ከፍታ ያለውን ታላቅ ሕንፃ መገንባት ከፈለጋችሁ፣ ወደ ታች ቆፍራችሁ ከመሠረት ትጀምራላችሁ። ይህ ትህትና ነው… ሕንፃው ከፍ ባለበት መጠን፣ መሠረቱ ወደ ታች መቆፈር አለበት” (Augustine †430)
√ “ለነፍሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ” (29)፥ … ትንቢተ ኤርምያስ 6፥16፥ “በየጎዳናው ቆማችሁ ተመልከቱ፤ ጥንታዊና መልካም የሆነችው መንገድ የትኛዋ እንደሆነች ጠይቃችሁ ተረዱ፤ ባገኛችኋትም ጊዜ በእርሷ ተጓዙ፤ ለነፍሳችሁ ሰላም ታገኛላችሁ”። ሰላም ማለት ይህን ጥንታዊ መንገድ ማገኘት ማለት ነው፥ ጥንታዊ መንገዱ የኢየሱስ መንገድ ነው፣ ወደ አብና ወደ ራሳችን እረፍት ቦታ የሚመራን የየዋህነትና የትህትና መንገድ ነው።
Leave a reply