
1ኛ ንባብ፥ የሐዋርያት ሥራ፥ 2,1-11
√ ነፋስ የሚመስለው ድምጽ ቤቱን ሞላው። እሳት ወርዶ በእያንዳንዳቸው ላይ አረፈ። ደቀመዛሙርቱም ወደ አደባባይ ወጥተው በተለያዩ ቋንቋዎች የእግዚአብሔርን ቃል መናገር ጀመሩ።
√ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ቃል ከመፅነስ በቀር ምንም ሌላ ተልእኮ የለውም። መንፈስ ቅዱስ ልክ በድንግል ማርያም ማህፀን ውስጥ ቃሉን በመፅነስ ልጅ እንድትወልድ እንዳስቻላት፣ አሁንም በሐዋርያት ላይ ራሱን በማፍሰስ በልባቸው ውስጥ ክርስቶስን እንዲፀንሱ፣ በሥራቸውም እርሱን እንዲያፈሩና ለአለም ሁሉ እርሱን እንዲያበስሩም ያስችላቸዋል።
“ዝግ በነበረ በላይኛው ክፍል በኩል የገባ መንፈስ፣ ኢየሱስ በተፀነሰበት ጊዜም ዝግ በነበረ በድንግል ማህፀን በኩል የገባ መንፈስ ራሱ ነው” (Gregory the Great †604)
የክርስትና ታሪክ እና የዘመናት ይዘት በትክክል የዚህ መለኮታዊ ፅንስና ልደት ማራዘሚያ ነው። የማርያም ሕይወት ፍሬ የኢየሱስ ልደት ነው። አጠቃላይ የቤተክርስቲያን ታሪክ ፍሬ እስከ ዓለም ዳርቻ የሚደርስ ክርስቶስ ነው። ነገር ግን የክርስቶስ ፍጻሜ በሐዋርያት ቃልና ስብከት መሰረት ይፈጸማል።
√ በሲና ተራራ ፊት ቃሉን በመስማት፣ እስራኤል አንድ አገር እንደሆነ፣ ነገዶች ሁሉ ቃሉን ሲያዳምጡ አንድ ሕዝብ ይሆናሉ።
አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት እስራኤልን እንደሚወክሉ ሁሉ። በጳራቅሊጦስ ቀን የተዘረዘሩት ነገዶች አሥራ ሁለት ናቸው።[1] ሐዋርያትም አሥራ ሁለት ናቸው፣ የተላኩበት አገራትም አሥራ ሁለት ናቸው። እንዲሁም አሕዛብ ሁሉ ከየአቅጣጫው ወደ ሰማያዊ ኢየሩሳሌም መውጣት ይችሉ ዘንድ፣ የምድር ሁሉ አቅጣጫዎች የሚያሳዩ የከተማይቱ በሮች አሥራ ሁለት ናቸው (ራእይ 21)።
√ ነፋስ ቤቱን ይሞላል። በሰው ውስጥ ሲሠራ እና በዓለም ላይ ሲሠራ፣ እግዚአብሔር የሚሞላ ሙላት ነው። ሰው ለእግዚአብሔር ስለተፈጠረ፣ እግዚአብሔር ብቻ ሊሞላው ይችላል። ሌላ ምንም ነገር ሊሞላው አይችልም፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረ በራሱ እንዲሞላ ነው።
“ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ… መናገርም ጀመሩ” (4)። ዝም ማለት አይቻልም። የእግዚአብሔር ኃይል አይገደብም። በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ አሥራ ሁለት ሰዎች ይናገሩና ዓለምን በእሳት ያቃጥላሉ፥ “በእርሱ የተነሳ ይቃጠላሉ፤ ስለ እርሱ ይናገራሉ” (Bede †735)። የቤተክርስቲያን ተልእኮ ምንጭ ከሰው ልብ የሚፈስ የዚህ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ነው። ምኞቱ አጽናፈ ዓለም ነው፣ ማብቅያው የዘመናት ፍፃሜ ነው።
√ መንፈስ ነፋስና ነበልባል ነው። ነፋስ የማይቻል ኃይል ነው። ከሰማይ ሆኖ (2)፣ ቤቱን በሙሉ ይሞላል (2)። ከዚያም አጽናፈ ሰማይን ይሞላል።
> በትንቢተ ሕዝቅኤል፣ ነቢዩ በሙታን አጥንቶች ወደ ተሞላ ሜዳ ከተወሰደ በኋላ፣ እግዚአብሔር፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ለመንፈስ ትንቢትን ተናገር፥ መንፈስ ሆይ ከአራቱም ማእዘን ና” ብሎ ያዘዋል (ትንቢተ ሕዝቅኤል 37፥9)። የሙታን ሙላት በመንፈሱም ተይዞ ለጦርነት እንደተዘጋጀ ሠራዊት ይነሳል።
ነፋሱ በኢየሩሳሌም ላይ ያርፍና ከማርያም ጋር ያሉት እነዚህ ደቀመዛሙርት ተነስተው ለጦርነት እንደተዘጋጀ ሠራዊት ይሆናሉ። በፊት በላይኛው ክፍል ውስጥ ተሰብስበው ህይወት እንደሌላቸው እጥንቶች ነበሩ። አሁን ግን መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ሊታሰሩ አይችሉም።
> በኦሪት ዘፍጥረት፣ ሰዎች ሰማይን ለመግዛት ሲሉ በእግዚአብሔር ላይ አምፀው ነበር (የባቢሎን ግምብ ምእራፍ 11)። ሰዎች በራሳቸው ኃይል ወደ ሰማይ መውጣት ሞክረው ነበር።
ዛሬ ግን እግዚአብሄር ከሰማይ በእየሩሳሌም ላይ ያርፍና፣ ሰማይ በምድር ላይ ወርዶ ይስፋፋል። አሕዛብ ሁሉ የተከፋፈሉ ናቸው፥ “የጳርቴና የሜድ የኤለም ሰዎች…” (9)። በመንፈስ ቅዱስ ሥራ አማካየነት ግን ለሁሉ አንድ አይነት ቃል ይደርሳል እና በራሱ ቃል ብሔራት ሁሉ አንድ እምነት ብቻ ስላላቸወ አንድ ሕዝብ ይሆናሉ።
√ ይህ ሁሉ ያለፈ ብቻ አይደለም። ዛሬም የቤተክርስቲያ ሕይወት እንዲሁ የመንፈስ ቅዱስ መምጣትና መፍሰስ ነው።
ራስህን ለመንፈስ ቅዱስ ግፊት በትህትና በማስረከብ፣ በእርሱም ተገዝተህ፣ ከእንግዲህ የራስህን ህይወት በመተው የክርስቶስን ሕይወት ኑር። እኛ የእግዚአብሔር ልጆች የምንሆነው በመንፈስ በምንማረክበት መጠን ነው። ነገር ግን ከባድ ስለሆንን (የእኛ ዝንባሌ ወደ ታች ስለሚገፋን)፣ መንፈሱ ብርቱ ነፋስ መሆን አለበት።
[1] “(1) የጳርቴና (2) የሜድ (3) የኤለም ሰዎች፥ (4) በሁለት ወንዝም መካከል በይሁዳም (ይህ በኋላ የተጨመረ ማብራሪያ ነው) (5) በቀጰዶቅያም (6) በጳንጦስም (7) በእስያም፥ (8) በፍርግያም (9) በጵንፍልያም (10) በግብፅም (11) በቀሬናም በኩል ባሉት በሊቢያ ወረዳዎች የምንኖር፥ (12) በሮሜም የምንቀመጥ፥ አይሁድም ወደ ይሁዲነትም የገባን፥ የቀርጤስና የዓረብ ሰዎች (ቀርጤስና ዓረብ የምዕራብና የምስራቅ ማጠቃለያ ናቸው)፥ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን” (2፥9-11)
Leave a reply