የኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት (A-PHASIKA-Ascension)

የኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት (A-PHASIKA-Ascension)

1ኛ ንባብ፥ የሐዋርያት ሥራ 1,1-11

√ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ኢየሱስ ከደቀመዛሙርቱ አይን ተለይቶ ቀረ። እስከዚያ ቀን ድረስ እየሱስ ከደቀመዛሙርቱ ጋር ይኖርና ይበላ ነበር፤ በገሊላ መንገዶች ላይም ከእነርሱ ጋር ይራመድ ነበር፣ ድምጹን ለመስማት እና ተዓምርን ለማግኘት ብዙ ሕዝብ በዙሪያው ይሰባሰቡ ነበር። አሁን ግን ከእነርሱ ተለይቶ ቀርቷል።

ነገር ግን እየሱስ ደቀመዛሙርቱን አልተወም፣ ይልቁን በውስጣቸው መኖር ጀምሯል። ካረገ በኋላ እየሱስ ከአይናቸው ቢለይም በነፍሳቸው ውስጥ መኖር ጀምሯል። በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ክርስቶስ በደቀመዛምርቱ ይኖራልና ደቀመዛሙርቱም በእርሱ ይኖራሉ። “በእኔ ኑሩ፣ እኔም በእናንተ እኖራለሁ” የሚል የኢየሱስ ቃል እና ትእዛዝ እንደሁ ተፈጽሟል (ዮሐንስ 15፥4)።

√ ደቀመዛሙርቱ ኢየሱስን ሲያናግሩ ለመጀመርያ ጊዜ “ጌታ ሆይ!” ብለው ይጠሩታል (6)። ‘ጌታ’ በግሪክ ቋንቋ ‘ኪርዮስ’ (κύριος) ይባላል። ‘ኪርዮስ’ ማለት ደግሞ በሲና ተራራ ላይ እግዚአብሐር ለሙሴ የገለጸለት ስም ነው። ይህ ስም በብሉይ ኪዳን ማንበብ የተከለከለ ስለነበረ፣ አይሁዶች በዚህ ስም መጠቀም አይችሉም ነበር። ከሞት ከተነሳ በኋላ ግን ይህ ስም ኢየሱስ የሚጠራበት ስም ሆኗል። ከእንግዲህ መምህርና ወዳጅ የሚል ቀርቶ (ዮሐ 15፥15፥ “ወዳጆቼ ብያችኋለሁ”)፣ ወንድም የሚልም ቀርቶ (ዮሐ 20፥17፥ “ወደ ወንድሞቼ ሂጂ”)፣ ኢየሱስ ‘ጌታ’ ተብሎ ይጠራል (ኪርዮስ)። ኢየሱስ ጌታ ነው፣ ኢየሱስ በሲና ተራራ ላይ የተገለጸ አምላክ ልጅ ነው።

> እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለደቀመዛሙርቱ የማሪያም ልጅ፣ የናዝሬቱ መምህር፣ ከበሽታ የሚፈውስ ጓደኛቸውና እረኛቸው ነበረ፣ አሁን ግን ጌታ ሆኗል። ይህ ቋንቋ ተራ ቋንቋ እንዳይመስለን፣ ትልቅ ነገር ይገልጻል። ለአይሁዶች፣ እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር የሚሽርና ስሙ ሊጠራ የማይችል አምላክ ነበረ። አሁን ግን ደቀመዛሙርቱ ኢየሱስን ‘ጌታ’ በማለት ይጠሩታል፥ ክርስቶስ የሲና አምላክ ስም ወስዷል! እንዲሁ የሐዋርያት ቋንቋ “እኔ ከእናንተ ጋር እሄዳለሁ፤ አምላካችሁ እሆናለሁ፣ እናንተም ሕዝቤ ትሆናላችሁ” የሚሉትን የእግዚአብሔር ቃላት አፈፃፀም ይገልጻል (ዘለዋውያን 26፥12)።

√ እግዚአብሔርን በሰማይ ውስጥ መፈለግ የለብንም፣ ሰማይ በረሐ ነው! ቅድስት Julian of Norwich (England †1416) አንድ ቀን “ወደ ላይ፣ ወደ ሰማይ ተመልከቺ” የሚላት ድምጽ ሰምታ፣ “ሰማይን ማየት አልፈልግም፣ ኢየሱስን ማየት እፈልጋለሁ” ብላ መለሰች (Revelations of Divine Love)። ምክንያቱም ሰማይ ባዶ ነው፣ እግዚአብሔር ግን ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ነው፣ እግዚአብሔር ለእኛ ሲል ሰው ሆኗል!

> ክርስትና ከዚህ ይጀምራል። ክርስትና የሚጀምረው ክርስቶስ እንደ አምላክ መታወቅ ከጀመረበት ጊዜ ነው። በያዕቆብ ጉድጓድ አጠገብ ደክሞ የተቀመጠ፣ በጀልባ ላይ ሲተኛ የታየ፣ ከእኛ ጋር የበላና የጠጣ አምላክ ነው! አንድ ጊዜ እግዚአብሔር ወደ አብርሃም ድንኳን ወርዶ ነበረ። ያን ጊዜ አመጣጡ ድንገጥ ነበረ። አሁን ግን መቆየቱ እንደሚያልፍ እንግዳ አይደለም፥ አሁን እግዚአብሔር ለእኛ ከራሳችን በላይ ለራሳሳችን ቅርብ ሆኗል፣ የነፍሳችን ጓደኛ ሆኗል።

√ “ጊዜው አሁን ነውን?” ብለው ይጠይቁታል (6)። ደቀመዛሙርቱ የመጨረሻ ድርጊት ማለትም የሁሉም ነገር የመጨረሻ ፍፃሜን ይጠብቃሉ። ኢየሱስን ከሙታን ተነስቶ ባዩት ጊዜ፣ እነርሱ ይህ ዓለም አሁን ይጠፋል ብለው ያስባሉ። ክርስቶስ ከሙታን ከተነሳ በኋላ፣ በየንጋቱ ፀሐይ አሁንም መውጣቷ፣ ያለማቋረጥ ወንዞች አሁንም መፍሰሳቸው፣ ሰዎች አሁንም መራባቸውና መጠማታቸው ለምን አስፈለገ? ትንሣኤ የሁሉ ነገር ፍጻሜ መሆን ነበረበት ብለው ያስቡ ነበር።

ኢየሱስ፥ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ… እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” (8) ብሎ ይመልሳል። ከኢየሱስ ትንሣኤ እና ክብር በኋላ፣ ሐዋርያት እዚህ በምድር ላይ የመኖሩ መለኮታዊ ምስክሮች ናቸው። በዚህ ምክንያት ኢየሱስ “ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” የሚለውን የተቀደሰ ትእዛዝ ይሰጣቸዋል፥ ። በእነዚህ ቃላት፣ ክርስቶስ ከትንሣኤ እስከ ዳግማዊ ምጽአቱ ድረስ ያለው የጊዜ ይዘት ይገልጻል። የሰው ታሪክ ጊዜና ሕይወት ከመመሥከር ውጪ ሌላ ምንም ይዘት የለውም። እስከአለም ዳርቻ ሰዎች ሁሉ ኢየሱስ ከሙታን እንደተነሳ እንዲያውቁ፣ የእኛ ሕይወት በሙሉ ለራሳችን መኖር ቀርቶ ለኢየሱስ ብቻ መኖር ሆኗል። ክርስቶስ ተነስቷልና ከእኛ ጋር ይኖራል።

Leave a reply