የፋሲካ 4ኛ እሁድ (A-Phasika-4)

የፋሲካ 4ኛ እሁድ (A-Phasika-4)

ወንገል፥  ዮሐንስ 10፥1-10

√ ወደ በጎች በረት በበር የማይገባ ሰው ሌባና ዘራፊ ነው (1)፥ መንጋውን ቀስ ብሎና በድብቅ መጉዳት ይቻላል፣ ወይም በግልጽና ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም መጉዳት ይቻላል። የክርስቶስ ጠላቶች በሁለቱም ዘዴዎች ተጠቅመው ያውቃሉ። “ውጭ ስንት በጎች አሉ፣ ውስጥ ስንት ተኩላዎች አሉ? ውስጥ ስንት በጎች አሉ፣ ውጭ ስንት ተኩላዎች አሉ?” (Augustine of Hippo †430)

√ እረኛ የራሱን በጎች በየስማቸው ይጠራቸዋል (3)፣ በጎቹም ድምጹን ስለሚያውቁ ይከተሉታል (3-5)፥ ምሽት ላይ ብዙ መንጋዎች በዘበኛ እየተጠበቁ ሌሊቱን በሙሉ ያድሩበት በነበረ በአንድ በረት ውስጥ ይሰበሰቡ ነበር። በማለዳ እያንዳንዱ እረኛ ወደ አጥሩ በር መጥቶ በጎቹን አንድ ላይ ይጠራል። በጎቹ ተሰብስበው በረቱን ትተው እረኛውን ይከተላሉ። በጎቹ እንዳይጠፉ ደጋግሞ እረኛው ድምፁን እያሰማ እነሱን ወደ መስክ ስፍራ ለመምራት ከፊት ለፊታቸው ይጓዝ ነበር። መለኮታዊ ትምህርት ለመግለጽ ጌታችን ኢየሱስ ለአድማጮቹ በጣም የታወቀ የነበረውን ይህ ምሳሌ ይመርጣል፥ ባልታወቁ ድምጾች መካከል የክርስቶስን ድምፅ እንዴት እንደሚለይ ማወቅ አስፈላጊ ነው።

> “እረኛህን ታውቃለህ እንዲሁም በእርሱ ትታወቃለህን? በበር በኩል በሚጠራበት ጊዜ ትከተለዋለህን? ወይስ እንደ ዘራፊና እንደ ከሐዲ አጥር ዘሎ የሚገባውን እንግዳ ሰው ትከተላለህ? በስውር የሚያጠፋህን የእንግዳ ድምፅ ትሰማለህን? ከእውነት ወደተራራዎች፣ ወደበረሐና ወደገደሎች እንዲሁም ጌታችን ወደማይጎበኛቸው ስፍራዎች የሚበታትንህን የእንግዳ ድምፅ ትሰማለህን? ከእውነተኛ እምነት ውጭ እንድትዘረፍ ትፈቅዳለህን?” (Gregory of Nazianzus †389)

√ በጎቹ የእረኛቸውን ድምጽ ይሰማሉ (3)።

> ወንጌል በግሪክ ቋንቋ ተጽፎአል፥ ‘በግ’ በግሪክ ቋንቋ ‘ፕሮባቶን’ ይባላል። ፕሮባቶን ደግሞ ‘ከሆነ ምንጭ ወደፊት የሚመጣ’ ማለት ነው (ፕሮ + ባይኖ = ወደፊት መምጣት)።

> ማንኛውን ነገር ከምን ወይም ከማን እንደሚመጣ ማወቅ እንፈልጋለን። ለምሳሌ ፍሬ ከግንብና ከዛፍ ሥሮች ይመጣል። ፍሬ ፍሬ የሆነው በውስጡ የሥሮቹን ሥራ ስለተቀበለ ነው። የፍሬ ሥራ የሥሮቹ ሥራ ነው፥ ፍሬ የሥሮቹን ሥራ በተቀበለ መጠን ከሥሮቹ ጋር አንድ ይሆናል። የፍሬ ምንጭ ሥሮቹ ናቸው።

የጀልባ ሸራዎች ይሠራሉ የሚባል በሚዘረጉበት ጊዜ ነው። የሚዘረጉት ግን የነፋስ ኃይል ሲሞላቸው ነው። ስለዚህ የጀልባ ሸራ ‘ከነፋስ ኃይል ወደፊት የመጣ’ ነው (ፕሮ + ባይኖ = ወደፊት መምጣት)። የጀልባ ሸራ የነፋስን ኃይል በተቀበለ መጠን ከነፋስ ጋር አንድ ይሆናል። የጀልባ ሸራዎች ምንጭ የነፋስ ኃይል ነው።

በተመሳሳይ ሁኔታ እኛም የምንጫችንን ኃይል በምንቀበልበት ጊዜ ከምንጫችን ጋር አንድ እንሆናለን፣ ‘ከምንጫችን ወደፊት እንመጣለን’ (ፕሮባቶን)።

> የዛፍ ሥር ሥራ በፍሬ ላይ ይፈስሳል። የነፋስ ኃይል ሥራ በጀልባ ሸራ ላይ ይፈስሳል። የእረኛ ሥራ በበጎቹ ላይ ይፈስሳል። የክርስቶስ ሥራ ሙሉ በሙሉ በተከታዮቹ ላይ ይፈስሳል።

ክርስቶስ በእኛ ላይ የሚፈሰስልን በምን አማካይነት ነው? በድምጹ ነው። ደቀ መዝሙርን የክርስቶስ በግ የሚያደርግ ወይም ‘ወደፊት እንዲመጣ’ የሚያነሳሳ የክርስቶስ ድምፅ ነው (በግሪክ ‘ፕሮባቶን’ = ከሆነ ምንጭ ወደፊት የሚመጣ = በግ መሆን ማለት ነው)። የክርስቶስ ድምፅ ደቀ መዝሙርን በክርስቶስ ሕይወት ሙሉ በሙሉ እንዲሳተፍ ያደርገዋል።

> ድምጽና ቃል አንድ አይነት ነገር አይደለም። ቃል ትምህርት ነው፣ ድምጽ ውበት ነው። እኛ በልማዳችን በድምጽ አማካይነት ለቃላታችን ውበትን እንሰጣለን። እግዚአብሔር በቃሉ ያሸንፍሃል፣ ነገር ግን በድምጹ ውበት ይማርክሃል።

ልጅ የእናቱን ድምፅ ለይቶ ይሰማል፣ በግ የእረኛውን ድምፅ ለይቶ ይሰማል። ነፍስህስ? የፈጣሪዋን ድምጽ ለይታ ትሰማለችን?

√ ኢየሱስ ደግሞ የበጎቹ በር መሆኑን ይናገራል (7)፥ ሁለቱም፣ እረኞችና በጎች፣ ወደ በረት መግባት ያለባቸው በክርስቶስ በኩል ነው። “ወደ እናንተ የምገባበት በር ክርስቶስ ነው። በክርስቶስ አማካይነት ወደ ቤታችሁ ሳይሆን ወደ ልባችሁ እገባለሁ። በክርስቶስ አማካይነት ገብቼ እናንተ በእኔ አማካይነት በደስታ ክርስቶስን ትሰማላችሁ። ለምን በእኔ በደስታ ክርስቶስን ትሰማላችሁ? የክርስቶስ በጎች ስለሆናችሁና በደሙ ስለተገዛችሁ ነው” (Augustine of Hippo †430)

Leave a reply