የፋሲካ 3ኛ እሁድ (A PHASIKA-3)

የፋሲካ 3ኛ እሁድ (A PHASIKA-3)

ወንገል፥  ሉቃስ 24፥13-35

√ ሁለት ደቀመዛሙርት (13)፥ አንዱ ቀለዮጳ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ አይታወቅም፣ በስሙ ፋንታ የእያንዳንዳችንን ስም መወከል እንችላለን። ሁለቱ ደቀመዛሙርት ይጓዙ ነበር፥ ሰው በምኞቱ ተመርቶ ሁል ጊዜ መንገደኛ ነው። እየተጓዙ እርስ በእርሳቸወ ይወያዩ ነበር (14)፥ እኛ የምንወያይ በልባችን ስላለው የምንመኘውና የምንወደው ነገር ነው።

√ ኢየሱስ ራሱ ወደ እነርሱ ይቀርባል (14)፥ ከሞት የተነሣ ክርስቶስ ወገኖቹን አይተውም፣ አሁን ለሁሉም ሰው እና በሁሉም ቦታ ለእነርሱ ቅርብ መሆን ይችላል። እንዲሁም በተዘጉ በሮች፣ በተሰወሩ አይኖች እና በደነደኑ ልቦች መግባት ይችላል። ወንጀለኛውን እስከ መስቀል ድረስ እንደፈለገ፣ አሁንም መንግሥቱን ይሰጠን ዘንድ እያንዳንዳችንን ይፈልጋል።

√ ኢየሱስ በቅዱሳት መጽሐፍት ሁሉ ስለ እርሱ የተነገረውን እየጠቀሰ ያስረዳቸው ነበር (27)፥ ቅዱሳት መጻሕፍት አንድ መጽሐፍ ብቻ ናቸው እናም ይህ መጽሐፍ ራሱ ነው፣ ምክንያቱም ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ስለ ክርስቶስ ይናገራሉና በእርሱ ፍፃሜን ያገኛሉ።

√ ከእነርሱ እንዳይለይ አጥብቀው ይለምኑታል (29)፥ ሰውን የሚፈልግ ፈጣሪ መለመን ይፈልጋል፣ ከእኛ ጋር እንዲሆን የሚያስገድደው ለእርሱ ያለን ፍላጎት ነው።

> ምሽት ገፍቶ ለስለስ ያለ ነፋስ ይነፍስ ነበር። በአካባቢው የደረሱ የስንዴ መስኮችና የቆዩ የወይራ ዛፎች ብራማ ቅርንጫፎች በምሽቱ ብርሀን ውስጥ ይታዩ ነበር። ጌታ ሆይ፣ ምንም የክብርህን ውጫዊ ምልክት ሳትለብስ በምትመጣበት ጊዜ አንተን መለየት እንድችል፣ አዲስ መንፈስ፣ ንፁህ ዓይንና ግልጽ አእምሮ ስጠኝ።

> መንገዳቸው በመንደሩ አቅራቢያ ይጠናቀቃል። ስጋ በለበሰ አምላክ ተደስተው፣ በልባቸው ጥልቀት በቃሉና በፍቅሩ የቆሰሉት ሁለት ደቀመዛሙርት ኢየሱስ አልፎ በመሄዱ ያዝናሉ። በእርግጥ አልፎ የሚሄድ ይመስላል (28)። እግዚአብሔር ራሱን ማስገደድ በጭራሽ አይፈልግም። በነፍሳችን ውስጥ ያስቀመጠውን ንፁህ ፍቅር በምናይበት ጊዜ በደስታና በፍላጎት እንድንጠራው ይፈልጋል። በኃይል መለመን አለብን ማለት ይቻላል፥ “ቀኑ መሽቶአል፣ ፀሐይም መጥለቅዋ ነው፤ ስለዚህ ከእኛ ጋር እዚህ ዕደር!” (29) (GREGORY OF NAZIANZUS †389)

ከእኛ ጋር እዚህ እደር (29)፥ ከእነርሱ ጋር ይኖር ዘንድ ለመኑት። “ከእኛ ጋር እዚህ እደር፣ ምክንያቱም ጨለማ ነፍሳችን ወረረና አንተ ብቻ ብርሃን ነህ። አንተ ብቻ የሚበላን ድካም ማረጋጋት ትችላለህ። ውበትና ክብር ካላቸወ ነገሮች ሁሉ መካከል የመጀመሪያው ለዘላለም ከአንተ ጋር መኖር ነው። (GREGORY OF NAZIANZUS †389)

> እግዚአብሔር በመካከላችን ማደሩ የቅዱስ ቁርባን ከፍተኛ ትርጉም ነው።

√ ከእነርሱ ጋር ሊያደር ወደ ቤት ይገባል፥ “እነሆ! እኔ በበር ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ደምጼን ሰምቶ በሩን ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ ገብቼ ከእርሱ ጋር እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል” (ዮሐንስ ራእይ 3፥20)። እና ደቀመዛሙርቱ ቂጣውን ሲቆርስ አይኖቻቸው ተከፍተው ኢየሱስ መሆኑን ያውቃሉ (31)፥ “በእግዚአብሔር መንግሥት በማእድ መቀመጥ የሚችል እንዴት የታደለ ነው!” (14፥15)።

እርሱ ግን ወዲያው ከዓይናቸው ተሰወረ፥ ኢየሱስ ከዓይናችን የሚሰወረው ከእነርሱ ጋር መኖር ቀርቶ በእነርሱ ውስጥ መኖር ስለሚጀምር ነው። ኢየሱስ ከእነርሱ በአካል ተሰውሮ የተለየ፣ በእምነት ስለጨበጡት ነው። (AUGUSTINE OF HIPPO †430)

√ እጅግ ተደሰቱ፥ “ልባችን እንደ እሳት ይቃጠል አልነበረምን?” (31)፥ በሲና ተራራ ላይ በሚነድ ቁጥቋጦ እንደነበረ፣ አሁንም በሚነድ ልባችን ውስጥ እግዚአብሔር ራሱን በመግለጽ የራሱንና የእያንዳንዳችንን እውነተኛ ስም ይናገራል። እግዚአብሔር ከእንግዲህ ከውጪ ሳይሆን በውስጣችን ይገለጻል፣ እውነተኛም ሕይወታችንን ይገልጽልናል።

√ እነርሱ በዚያችው ሰዓት ተነሡና ወደ እየሩሳሌም ተመልሰው ሄዱ (33)። ኢየሱስ በተሰቀለበት ሰዓት እኩለ ቀን ላይ ፀሐይ ጨልማ ነበር፤ በተቃራኒው የመሸ በሚመስለው በደቀመዛሙርት ቀን ፀሐይ በፍፁም መጥለቅ አትፈልግም። ምክንያቱም ፀሐይ በነፍሳቸው ውስጥ ገብታ ነበረ። “እንደዚህ ያለ ቀን ከዚያም በፊት ሆነ ከዚያ ወዲህ ታይቶ አይታወቅም፥ ጸሐይ በሰማይ መካከል ቆመ፣ ቀኑንም ሁሉ ሳይጠልቅ ቆየ” (ኢያሱ 10፥12-14)።

ስለ ሁሉ ነገር ተረኩላቸው (35)፥ ሌሊት ገብቶአል፣ ነገር ግን ለሌሎች ስለ እርሱ መናገር አለብን፣ ምክንያቱም ይህን ለሚያክል ደስታ አንድ ልብ ብቻውን አይበቃም። ከኢየሩሳሌም ስንወርድ ሕያው አምላክ ቀረበን። እርሱ አይቶናል፣ ወደ እኛ ቀርቦ በዘይቱና በወይኑ አክሞናል። በቃሉ ልባችን ተቃጥሎአል፣ በሕብስቱ ሲለዩት አይኖቻችን ተከፍተዋል። ከዚህ ወዲህ እርሱ በእኛ፣ እኛም በእርሱ እንኖራለን። የእኛ መንገድ የእርሱ መንገድ ሆኖአል፥ ወደ ኤማሁስ… ጌታችን የዚህን መንደር ስም እንዴት ጣፋጭ አድርጎአል!

Leave a reply