[WW3] የመስቀል ርዕስ (Titulus Crucis)

[WW3] የመስቀል ርዕስ (Titulus Crucis)

“ጲላጦስ የናዝሬቱ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ የሚል ጽሑፍ ጽፎ በመስቀሉ ራስጌ ላይ አኖረው። ኢየሱስ የተሰቀለበት ስፍራ ለከተማ ቅርብ ስለነበረ፣ ከአይሁድ ብዙዎቹ ጽሑፉን አነበቡት፤ ጽሑፉም የተጻፈው በዕብራይስጥ በላቲንና በግሪክ ቋንቋ ነበረ” (ዮሐንስ 19፥19-20)

⇒ ወንጌላዊው ዮሐንስ በመስቀሉ ላይ የተጻፈው ጽሑፍ በዕብራይስጥ፣ በላቲንና በግሪክ ቋንቋ መሆኑን ሊነግረን ለምን ፈለገ? ለዚህ መልስ ለመስጠት፣ በመጀመሪያ በብሉይ ኪዳን ጊዜ በእግዚአብሔር ስም ዙሪያ የነበረ የቅድስናን ግንዛቤ መመልከት ያስፈልጋል።

በኦሪት ዘጸአት መጽሐፍ ውስጥ እንደሚነበብ፣ በሲና ተራራ ላይ ራሱን በገለጸበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር ህዝቡን ከግብጻዊያን ቀንበር ነፃ እንዲያወጣ ሙሴን አዘዘ። በዚህ ታላቅ ትእዛዝ ፊት፣ ሙሴ ብዙ ጥያቄ ያቀርባል፥ ሕዝቡን እንዴት ያሳምናል? የእግዚአብሔር ስም ማን ነው? “እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፥ ‘እኔ ያለሁና የምኖር ነኝ’፤ ስለዚህም ‘እኔ ነኝ ወደ እናንተ ልኮኛል’ በላቸው” (አሪት ዘጸአት 3፥14)። ትምህርተ ክርስቶስ እንደሚያስተምረው፣ ይህ ስም “እግዚአብሔር የሕላዊና የሁሉ ፍጡራን መነሻና መድረሻ የሌለው ምክንያት እና የሕላዊና የሁሉ ፍጻሜ ሙላት መሆኑን ይገልጻል” (CCC 213)።

‘እኔ ነኝ’ የሚል የእግዚአብሔር ስም በጣም ታዋቂ በነበሩት በአራት ቅዱሳት ፊደላት ይጻፍ ነበር። እንሆ እነዚህ ናቸው፥ ይ – ህ – ው – ህ ወይም YHWH። እነዚህ አራት ፊደላት ግን እንዴት እንደሚነበቡ አይታወቅም፣ ምክንያቱም እጅግ በጣም ቅዱስ ስለነበረ፣ ሁለተኛ ቤተመቅደስ ከተገነባ በኋላ የእግዚአብሔር ስም ተነቦ አያውቅም። በርሱ ፈንታ ‘አዶናይ’ የሚል የነበብ ነበር (በግሪክ ቋንቋ አዶናይ ማለት ‘ኩርዮስ’፣ በአማርኛ ‘ጌታ’ ማለት ነው)

⇒ አሁን ደግሞ ወደ አዲስ ኪዳን እንመለስ። ሐዋርያ ዮሐንስ ኢየሱስ “የሰውን ልጅ ከፍ አድርጋችሁ በምትሰቅሉት ጊዜ እኔ ‘እኔ ነኝ’ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ” የሚል ትንቢት እንደተናገረ ጽፎ ይመሰክራል (ዮሐንስ 8፥28)። ስለዚህ ኢየሱስ ከፍ ብሎ በሚሰቀልበት ጊዜ የአባቱን ስም ይገልጻል ማለት ነው።

ወደ ስቅለት ቀን እንመለስ። በመስቀል ራስጌ ላይ በሦስት ቋንቋ ስለተጻፈው ጽሑፍ ሲነግረን፣ ሐዋርያ ዮሐንስ “ኢየሱስ የተሰቀለበት ስፍራ ለከተማ ቅርብ ስለነበረ፣ ከአይሁድ ብዙዎቹ ጽሑፉን እንዳነበቡት” ጽፎ ያስታውቀናል። ስለዚህ ጽሑፉ በጣም የሚታይ ነበረ። በዚህም ምክንያት የካህናት አለቆች ጲላጦስን፥ “የአይሁድ ንጉሥ ብለህ አትጻፍ፤ ነገር ግን፥ ይህ ሰው ‘እኔ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ ብሎአል’ ብለህ ጻፍ” ብለው ጨቀጨቁት። በዚያ ጽሑፍ ላይ የካህናትን አለቆች የሚረብሻቸው ትልቅ ጭንቀት ተፈጠረ!

በካህናት ፊት በተፈረደበት ጊዜ፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ የካህናት አለቃ ልብሱን እንደቀደደ ማስታወስ እንችላለን። የካህናት አለቆች፣ ኢየሱስ ሰው ሆኖ ራሱን አምላክ ማድረግን እንደ ኃጢአት ይቆጥሩ ነበር።

⇒ INRI የላቲን ጽሑፍ ነበረ፤ የዕብራይስጥ ጽሑፍ ግን ምን የሚል ነበረ? በብዙ ምሁራን ጥናት አማካይነት (በተለይ Henri Tisot 1937-2011)፣ “የናዝሬቱ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ጽሑፍ ትክክለኛ የዕብራይስጥ ፊደላት ተረጋግጠዋል። እንሆ ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፥ היהודים ומלך הנוצרי שועי። እያንዳንዱ ፊደል ወደ ግዕዝ ፊደል ሲቀየር እና ከቀኝ ወደ ግራ ሲነበብ፣

ሹዓ

ኖጽሪ

መለክ

የሁዲም”

(ወይም Yeshua Hanotsri Wemelek Hayehudim) የሚል ጽሑፍ እናገኛለን። የጽሑፉ አራት ቃላት የመጀመሪያ ፊደላት ደግሞ በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ የተገለጹ አራቱ ቅዱሳት ፊደላት ይሰጡናል፥

– ይሹዓ

– ህኖጽሪ

– ውመለክ

– ህየሁዲም”

ወይም YHWH ወይም “እኔ ነኝ”። የኢየሱስ ትንቢት እንዲሁ ተፈጽሞአል።

በክርስቶስ ያላመኑት አይሁዳዊያን ልክ ኢየሱስ በተዋረደበት ሰዓት በዓይናቸው ፊት ያልተቀበሉትን እውነት ስላነበቡ፣ ጲላጦስ ጋር ተጨቃጨቁ። የጲላጦስ መልስ እናውቃለን፥ “የጻፍኩትን ጽፌያለሁ” የሚል ነበረ (ዮሐንስ 19-22)።

የክርስቶስን መለኮት መካድ የሁሉ ክሕደት ምንጭ መሆኑን ስለምናውቅ፣ ይህ የተፈጸመ ትንቢት እስከ መስቀል ድረስ በማይነገር ፍቅር የወደደንና የሚወደን አምላክ አስታውሰን እንድንደሰት ያደርጋል።

Leave a reply