[UR5] ኮቪድ-19 እና የእግዚአብሔር ቅጣት (1)

[UR5] ኮቪድ-19 እና የእግዚአብሔር ቅጣት (1)

ኮቪድ-19 ስለእግዚአብሔር ቅጣት እንደገና እንድናስብ እያደረገ ነው፥ ነገር ግን ከቅዱሳት መጻሕፍት ጀምሮ ጉዳዩ ውስብስብ ነው። እግዚአብሔር ይቀጣልን? ለመረዳት እንሞክር።

የመጀመሪያው መልስ በ2ኛ ጴጥሮስ 2፥4-17 ላይ እናገኛለን፥ “መላእክትን እንኳ ኃጢአት በሠሩ ጊዜ እግዚአብሔር ሳይራራላቸው በጨለመ ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ሆነው የፍርድን ቀን እንዲጠባበቁ ወደ ገሃነም ጣላቸው፥ እንዲሁም የጽድቅ ሰባኪ የነበረውን ኖኅን ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር አድኖ እግዚአብሔርን የማያመልኩ ሰዎች በነበሩበት አለም ላይ የጥፋትን ውኃ ሲያመጣ ራርቶ የቀደመውም ዓለም አልማረውም፤ ደግሞ እግዚአብሔርን ለማያመልኩ ሁሉ የመቀጣጫ ምሳሌ እንዲሆኑ የሰዶምንና ገሞራን ከተሞች ዐመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎ እንዲጠፉ ፈረደባቸው… ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር በየቀኑ ያየውና ይሰማው በነበረው ሕገ ወጥ ድርጊታቸው ጻድቅ ነፍሱ ትጨነቅ ነበር… ጌታ እግዚአብሔር እርሱን በማምለክ የሚኖሩትን ሰዎች ከፈተና እንደሚያድናቸው፥ ኃጢአተኞችንም እንዴት እንደሚቀጣና ለፍርድ ቀንም እንዴት ጠብቆ እንደሚያቆያቸው ያውቃል ማለት ነው… እነዚህ ግን ለመጠመድና ለመገደል እንደ ተወለዱ በተፈጥሮ ስሜት እንደሚኖሩና አእምሮ እንደሌላቸው እንስሶች ናቸው፤ እንስሶች እንደሚጠፉ እነርሱም ፈጽመው ይጠፋሉ። በደል ስለፈጸሙ ዋጋቸውን ይቀበላሉ… ነውረኞችና ርኵሳን ሆነው ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣ ይዘፍናሉ፤ ኃጢአትን ከማድረግ የማይቆጠብ ቅንዝረኛ ዐይን አለአቸው… መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው… የተረገሙ ናቸው። እነርሱ የቀናውን መንገድ ትተው ጠፍተዋል…  እነዚህ ሰዎች ውኃ የሌለባቸው ምንጮች ናቸው፤ በዐውሎ ነፋስ የተነዱ ደመናዎች ናቸው፤ ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም ይጠብቃቸዋል”።

የዚህ መግለጫ ታላቅነት የምናየው ኃጢአትንና የእግዚአብሔርን ቅጣት አንድ ላይ በማምጣት ሳይሆን፣ ከመላእክት በመጀመር ነው፥ የእግዚአብሔር ቅጣቶች ገና ሰው ከመፈጠሩ በፊት ይጀምራሉ!

የአዳም ኃጢአት በኃጢያትና በቅጣት መካከል ያለውን የመጀመርያ ግንኙነት ያስቀምጣል። በትምህርተ ክርስቶስ መሰረት (CCC 399-400)፣ የእግዚአብሔር “እርግማኖች” ዝርዝር በኦሪት ዘፍጥረት 3፥14-19 ላይ ይጠቀሳል፥ በመጀመሪያ የነበረውን ቅድስናና ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ወዳጅነት ማጣት፣ በግል ህየወትና በወንድና ሴት መካከል ባለው ግንኙነት ውስጥ ደስታን ማጣት፣ ክፉን መመኘት፣ ከፍጥረት ጋር የነበረውን አንድነት ማጣትና ከሁሉ በላይ የሞት ሐዘን።

ይህ ሁሉ ግልፅ ነው። ከዚህ በኋላ ያለው ጥያቄ ግን የሚከተለው ነው፥ የሰው ዘር አሳዛኝ ሁኔታ የመነጨው በመጀመርያ የነበረ የፍጥረት ሚዛን በመበላሸት ብቻ ነው ወይስ በቅጣት መልክ የእግዚአብሔር ቀጥተኛ ጣልቃገብነት በመኖሩ ነው? በእርግጠኝነት እርግማኖች ከእግዚአብሔር አፍ የወጡ በመሆናቸው፣ ሁለቱ መልሶች ትክክለኛ እንደሆኑ እንድንገምት ያደርጋል፥ ብዙ ጊዜ በሰዎች መካከል ያለው አሳዛኝ ሁኔታዎች፣ የሰው ሕይወት ክብደትና የሞት ስቃይ የአዳም የኃጢአት ውጤት ናቸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የመለኮታዊ ቅጣት ውጤት ናቸው

አንዳንድ ጊዜ ብሉይ ኪዳን የተፈጥሮ አደጋዎችን፣ በሽታዎችን፣ ጦርነቶችንና የተሸነፉት አሳዛኝ ሁኔታዎችን የሚያየው ከእግዚአብሔር የመጣ ቅጣት እንደሆነ ነው።

ለምሳሌ የውሃ ጥፋት እንደ የእግዚአብሔር ሥራ ታይቶአል፥ “እግዚአብሔር የሰው ክፉት በምድር ላይ እንደ በዛ፥ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደ ሆነ አየ። ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፣ በልቡም አዘነ። እግዚአብሔርም፥ የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፥ ከሰው እስከ እንስሳ ተንቀሳቃሽም እስከ ሰማይ ወፍ ድረስ፤ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቼአለሁና አለ” (ዘፍጥረት 6፥5-7)። የውሃ ጥፋት በተለያየ መልክ ሊታይ ይችላል፥ መጽሐፍ ቅዱስ ግን የሚመለከተው እንደ እግዚአብሔር ቅጣት ነው።

በሰዶምና በገሞራ ኃጢአት ምክንያት፣ ነዋሪዎቹን ካሳወራቸው በኋላ፣ እግዚአብሔር “ከሰማይ እሳትና ዲን አዘነበ” (ዘፍጥረት 19፥11.24)። የእሳትና የዲን ዝናብ በተለያየ መልክ ሊታይ ይችላል፥ መጽሐፍ ቅዱስ ግን በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር የተላከ ቅጣት ነው ብሎ ይተረጉመዋል።

ወደግል ጉዳዮች ስናልፍ፣ ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር አመንዝራ ከፈጸመ በኋላ “እግዚአብሔር የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችውን ሕፃን በከባድ ሕመም ቀሠፈ”፣ ሕፃኑም “በሰባተኛው ቀን ሞተ”(2ኛ ሳሙኤል 12)። ዳዊት ደግሞ ሕዝብን በመቆጠር ኃጢአት ስለሠራ “እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ቸነፈር አመጣ”። በዳዊት ንስሐ ምክንያት ቸነፈሩ ተነስቶአል፣ ነገር ግን “ከሕዝቡም ሰባ ሺህ ሰው ሞተ” (2ኛ ሳሙኤል 24፥15)።

ሌላ ተሪካዊ ከስተት ደግሞ መመርመር እንችላለን፥ የደቡብና የሰሜን መንግስታት ውድቀት ወረራና ስደት። ይህ የተከሰተው “አምላካቸውን እግዚአብሔርን በድለው ስለነበረና፥ ሌሎችንም አማልክት አምልከው ስልነበረ” ነው (2ኛ ነገሥት 17፥7)። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር “ከፊቱ እስኪጥላቸው ድረስ በበዝባዦች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው” (2ኛ ነገሥት 17፥20)። የሁለቱ መንግሥታት ውድቀትና የሕዝብ ስደት በሌሎች ብዙ ታሪካዊና ፖሊቲካዊ መልኮች ሊገለጽ ይችላል፥ መጽሐፍ ቅዱስ ግን አሁንም እንደ እግዚአብሔር ቅጣት ያያቸዋል።

የእስራኤል ሕዝብ ከስደት ሲመለስ ረሃብና ድርቅ የደረሰበት የቤተመቅደስ ግንባታ ስልጓተተ ነው (ሐጌ 1፥5-11)።

አሁን ግን ወደ አዲስ ኪዳን ስንመለስ፣ ሦስት አቅጣጫዎች እናገኛለን።

አንደኛ፥ ኃጢያትና አካላዊ ጉዳት ቀጥታ ግንኙነት የላቸውም። ኢየሱስ ዓይነ ስውሩ ሲጠይቀው “የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም” (ዮሐንስ 9፥3) በማለት ይመልሳል። ከዚህ በላይ ግልጽ ሊሆን አይችልም!

ሁለተኛ፥ ሰዎች መጥተው ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስላደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች ኢየሱስን ሲጠይቁት፥ ኢየሱስ የሞቱት እሱን ከሚያዳምጡ በላይ ኃጢአተኞች እንዳልነበሩ ይገልጽላቸዋል። ነገር ግን “ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ” (ሉቃስ 13፥3)። ኢየሱስ አንድ የታመመ ሰው ከፈወሰ በኋላ አገኝቶት፥ “እነሆ፥ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ከእንግዲህ ወዲህ ኃጢአት አትሥራ” (ዮሐንስ 5፥14) ብሎ ይገስጸዋል። እነዚህ ቃላት ከአካል ጉዳት ወይም ከአደጋ ጋር የተዛመደ የቀድሞ ኃጢአት እንዳለ ያስገምታሉ። ቢሆንም ግን እዚህ ላይ የኢየሱስ ቃላት ዋና አላማ ከዚህ የባሰ የመጨረሻ ጉዳት የማስቀረት ነው።

ሦስተኛ፥ ሐዋርያ ጳውሎስ፥ በቆሮንቶስ ያለውን ተገቢ ያልሆነ የቅዱስ ቁርባን አቀባበል ሲያይ፣ “ከእናንተ መካከል ብዙዎች የደከሙትና የታመሙት አንዳንዶችም የሞቱት በዚሁ ምክንያት ነው” (1ኛ ቆሮንቶሰ 11፥30) ብሎ ጽፎአል። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ነውና በቅዱስ ቁርባን አቀባበልና በበሽታ መካከል ያለውን ቀጥተኛ ግንኙነት ያስቀምጣል። እዚህ ላይ የጳውሎስ ቃልና ኢየሱስ ለዓይነ ስውሩ የሰጠው ምላሽ   በትክክል ተቃራኒ ነው። ነገር ግን ጳውሎስን ከኢየሱስ ጋር ማጋጨት አስፈላጊ አይደለም፥ ይልቁንም የሰው ሁኔታዎች የተለያዩ መሆናቸውና የእግዚአብሔር መልስ በየጊዜው የተለያየ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ለማጠቃለል፣ አዲስ ኪዳን አንዳንድ ጊዜ በኃጢአትና በበሽታ መካከል ግንኙነት አለመኖሩን፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ግንኙነት መኖሩን ያስተምራል።

አሁን ደግሞ የእግዚአብሔር የቅጣት እርምጃ የተገለጠበትን የአዲስ ኪዳን ገጾች እንመልከት።

አንደኛ፥ ኮላዞ (“kolázô” = ወይን መግረዝ ወይም መቅጣት)። በማቴዎስ ወንጌል 25፥46 “እነዚያ ወደ ዘላለም ቅጣት”፣ በ2ኛ ጴጥሮስ 2፥9 እግዚአብሔር “ኃጢአተኞችን ይቀጣና ለፍርድ ቀንም ጠብቆ ያቆያቸዋል”። እዚህ ላይ ሁለት ነገር ማየት እንችላለን፥ ኃጢአትን በመሥራት የሚመጣ ሐዘንና የእግዚአብሔር የቅጣት እርምጃ።

ሁለተኛ፥ ቲሞረዎ (“timôréô” = ክብርንና ፍትሕን ወደነበረበት መመለስ)። ግልጽ መረጃ በዕብራውያን 10፥29 ውስጥ ይገኛል፥ “የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኵስ ነገር የቆጠረ የጸጋውንም መንፈስ ያስከፋ፥ እንዴት የባሰ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል?”

ሦስተኛ፥ ዲኬ (“díkê” = ፍትሕና በቀጪ እርምጃ ፍትሕን ወደነበረበት መመለስ)። ሰውነታችንን በቅድስና መያዝ አለብን ምክንያቱም “ጌታ ስለዚህ ነገር ሁሉ የሚበቀል ነውና” (1ኛ ተሰሎንቄ 4፥6)። የእየሩሳለም ጥፋት ጊዜ “የበቀልና የቅጣት ጊዜ ነው” (ሉቃስ 21፥22)። በጊዜአት መጨረሻ ኢየሱስ ከሰማይ ተገልጾ “እግዚአብሔርን የማያውቁትን፣ ለወንጌልም የማይታዘዙትን ይበቀላል” (2ኛ ተሰሎንቄ 1፥8-9)። “በቀል የእኔ ነው” የሚልም ዛሬ ይታወቃል (ዕብራውያን 10፥30)።

በመጨረሻም፥ ፓይደዎ (“paidéuô” = ማረም ወይም ማስተማር)። “የምትሰቃዩ እንድትታረሙ ነው፤ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው?” (ዕብራውያን 12፥7)። “እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ፣ እቀጣቸውማለሁ” (የዮሐንስ ራእይ 3፥19)። ነገር ግን ሁለት የሚያፅናኑ መግለጫዎችን እናገኛለን፥ “እግዚአብሔር ለእርሱ ቅርብ የሆኑትን የሚቀጣ ለማረም ነው እንጂ ለመበቀል አይደለም” (ዩዲት 8፥27)፤ “ቅጣት የሚሰጠው ሕዝባችንን ለማጥፋት ሳይሆን፣ እንዲታረም ነው” (2ኛ መቀባዊያን 6፥12)።

በአዲስ ኪዳን ግን፣ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው የመጨረሻ እቅድ ይገለጻል፥ “እግዚአብሔር ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን እንዲያውቁ ይፈልጋል” (1ኛ ጢሞቴዎስ 2፥4)። ይህ ሐሳብ በአንዳንድ የብሉይ ኪዳን ጽሑፎች ቀድሞ ይነበባል። እንደ ምሳሌ፣ “እግዚአብሔር በህያዊያን መጥፋት አይደሰትም” (መጽሐፈ ጥበብ 1፥13) እና “የሰውን ልጆች ከልቡ አያስጨንቅም አያሳዝንምም” (ሰቆቃው ኤርምያስ 3፥33)።

እግዚአብሔር ወንጀሎችን መዝግቦ ቅጣት የሚያስከትል ግድየለሽ ዳኛ አይደለም፥ እግዚአብሔር ከጎናችን ነው እና በመከራዎች አማካይነት ሊያድነን ይፈልጋል። ነገር ግን እግዚአብሔር “ኮስታራ አምላክ ነው” እና ነፃ አድርጎ ስለፈጠረን፣ እሱን ያለመቀበል ያለንን ነፃነት ያከብራል።

እስከዚህ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን አዳምጠናል። ከመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ግን መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬ ሁኔታችን እንዴት እንደሚፈጸም ወደሚገልጽልን ጥናት ማለፍ ያስፈልጋል። ለሚቀጥለው ጊዜ እንገናኝ።

ይቀጥላል…

Leave a reply