
ወንገል፥ ዮሐንስ 11፥1-45
ቁ3 “ጌታ ሆይ፥ እነሆ ወዳጅህ ታሞአል”፥ …
“ብዙዎች የእግዚአብሔር ወዳጆች በመጥፎ ነገር ሲሰቃዩ ማየት ያናድዳቸዋል። ለምሳሌ፣ የታመሙ ወይም ድሃ የሆኑ ወይም ሌሎች አሳዛኝ ሁኔታዎችን የተቋቋሙ አሉ። በዚህ ምክንያት የሚሰናከሉት የእግዚአብሔር ልዩ ወዳጅ እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች ለመቋቋም የእርሱ ድርሻ እንደሆነ አያውቁም። የአልዓዛርን ታሪክ ማየት እንችላለን፥ እርሱ የክርስቶስ ወዳጅ ነበረ ግን ታሞአል” (JOHN CHRYSOSTOM 344-407)
“እዚህ ላይ ለወዳጅ የሚያስፈልገው አንድ ትእዛዝ ብቻ ነው፥ ነገር ግን ሴቶቹ ኢየሱስን ’ና’ ብለው አላዘዙም። ደግሞም ‘እዚያ እዘዝ እና እዚህ ይፈጸማል’ ለማለት አልደፈሩም። እነዚህ ሴቶች የተናገሩት ‘ጌታ ሆይ፥ እነሆ የምትወደው ታሞአል’ የሚል ቃል ብቻ ነው፤ ማለትም፥ አንተ ማወቅህ በቂ ነው፣ ምክንያቱም ሰውን ወደህ ለብቻ አትተውም” (AUGUSTINE 354-430)
ቁ6 “እንደ ታመመም በሰማ ጊዜ ያን ጊዜ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ዋለ”፥ …
“ለሞት ሙሉ በሙሉ ቦታ እንዴት እንደሰጠ ትመለከታለህ። ኢየሱስ ለመቃብር ነፃ ግዛትን ይሰጣል። የስጋ ብልሽት እንዲኖር ይፈቅድለታል። የስጋ መበስበስና ክርፋት የለመደውን አካሄድ እንዳያቆም አይከለክልም። የጨለማ ዓለም ጓደኛውን ይዞ ወደ ሲኦል እንዲወስደው ይፈቅድለታል። ኢየሱስ ይህን ሁሉ የሚያደርገው የሰዎች ተስፋ ሙሉ በሙሉ ወደ ዝቅተኛ ጥልቀት ገብቶ እንዲጠፋና፣ የሚያከናውነው ሥራ ከሰው ሳይሆን ከእግዚአብሔር እንደሆነ በግልፅ እንዲታይ ነው” (PETER CHRYSOLOGUS 380-450)
ቁ9-10 “ኢየሱስም መልሶ፥ ቀኑ አሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን? በቀን የሚመላለስ ቢኖር የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና አይሰናከልም፤ በሌሊት የሚመላለስ ቢኖር ግን ብርሃን በእርሱ ስለ ሌለ ይሰናከላል አላቸው”፥ …
“ሰዎች ለእግዚአብሔር፣ ደቀመዛሙርት ለመምህር፣ አገልጋዮች ለጌታቸው፣ ህመምተኞች ደግሞ ለሐኪማቸው ምክር ለመስጠት በደፈሩበት ጊዜ፣ ጌታችን ኢየሱስ ገሰጻቸው። አሥራ ሁለት ደቀመዛሙርት በመምረጥ እርሱ ራሱ ቀኑ መሆኑን አሳይቷል። እኔ ቀን ከሆንኩና እናንተ ሰዓታት ከሆናችሁ፣ ሰዓታት ለቀኑ ምክር ለመስጠት ይገባቸዋልን? ሰዓት ቀኑን ሳይሆን ቀን ሰዓቱን ይመራል። ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ አስራ ሁለት ደቀመዛሙርትን የመረጠ በዘፈቀደ ሳይሆን፣ እሱ ራሱ መንፈሳዊ ቀን መሆኑን ለመግለጽ ነው። በሰዓታት ስብከት አማካይነት አለም በቀኑ ማመን እንዲችል፣ ደቀመዛሙርቱ ሰዓታት ናቸው፥ ሰዓታት ቀኑ በሰዓታት ላይ ብርሃኑን ያብራላቸወ” (AUGUSTINE 354-430)
ቁ14 “አልዓዛር ሞተ”፥ …
“ማንኛውም ሐኪም በሽተኛው እንዳይሞትበት ይደክማል። የአልዓዛር ሐኪም ግን በሞት ላይ ድል ለማሳየት ስለፈለገ መሞቱን እየጠበቀ ነበር” (EPHREM THE SYRIAN 306-373)
ቁ25 “ኢየሱስም፥ ትንሣኤና ህይወት አኔ ነኝ”፥ …
“ሙታንን የሚያስነሳ የሕይወት ድምፅ እኔ ነኝ። ሐዘንና ለቅሶን የሚያስወግድ መልካም ሽቶ እኔ ነኝ። የእኔ የሆኑት ሁሉ ደስታ ተሰጥቷቸዋል። የአለም ሁሉ ደስታ ደግሞ እኔ ነኝ። ጓደኞቼን ሁሉ ደስ አሰኛቸዋለሁ፣ እንዲሁም ከእነሱ ጋር እደሰታለሁ። የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ” (ATHANASIUS 297-373)
ቁ26 “ሕያው የሆነም በእኔ የሚያምን ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፥ ይህን ታምኚያለሽን? አላት”፥ …
“መቀበር የነበረበት አንድ የሞተ ሰው ነበረ፣ የመተውን ለመቅበር የመጡ የሞቱ ሰዎች ነበሩ፣ አንዱ በስጋ ሞቶ ነበር፣ ሌሎቹ በነፍስ ሞተው ነበር። ሞት ወደ ነፍስ የሚመጣው እምነት ሲጎድል ነው። ሞት ደግሞ ወደ ሥጋ የሚመጣው ነፍስ ሲጎድል ነው። ምክንያቱም እምነት የነፍስ ሕይወት ናትና” (AUGUSTINE 354-430)
ቁ35 “ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ”፥ …
“እግዚአብሔር በሰዎች እንባ ተነሳስቶ አለቀሰ፣ እናም ኃይሉን በመዘርጋት አልዓዛርን ከሞት እስራት ቢፈታውም ቅሉ፣ በሚያፅናና በፍቅሩ እምባ አማካይነት የሰውን ፍቅር አገላለጽ አሟልቷል። በእንባና በርኅራኄ የሰው ልጆች የሚያደርጉትን እንዲያደርግ እግዚአብሔር አለቀሰ። የሰው ተፈጥሮ ከዘላለማዊነት ከተባረረ በኋላ የታችኛውን ዓለም ነገሮች መውደድ እስከሚችል ደረጃ ድረስ ስለወደቀ፣ እግዚአብሔር አለቀሰ። የማይሞቱ መሆን ይችሉ የነበሩት የሰው ልጆች ዲያቢሎስ ሟች ስላደረጋቸው እግዚአብሔር አለቀሰ። ብዙ ጥቅሞች ተሰጥተዋቸው የነበሩት ሰዎች ዲያቢሎስ ኃጢአትን በማስተማር ከሞላው ደስታ ስላስወገዳቸው እግዚአብሔር አለቀሰ” (POTAMIUS OF LISBON 360)
“የኢየሱስ እንባ እንደ ዝናብ፣ አልዓዛር እንደ ስንዴና መቃብሩ ደግሞ እንደ ምድር ነበረ። ኢየሱስ እንደ ነጎድጓድ ጮኸ፣ ሞት በድምፁ ተንቀጠቀጠ። አልዓዛር እንደ ስንዴ ከምድር ወጣ። ወጥቶም ከሞት ያስነሣውን ጌታው ሰገደ” (EPHREM THE SYRIAN 306-373)
ቁ38 “ኢየሱስም እያዘነ ወደ መቃብሩ ሄደ፤ እርሱም ዋሻ ነበረ፤ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር”፥ …
“ይህን አደረግሁ፣ እግዚአብሔር ግን አድኖኛል። ይህን አደረግሁ፣ እግዚአብሔር ግን ከእኔ ጋር ሆኖአል። ወንጌልን ሰምቼ ችላ ብያለሁ። ተጠምቄ እንደገና ወደ ድሮ ልምዶቼ ተመለስኩ። ምን እያደረግኩ እንደሆነ አላውቅም? ወዴት እሄዳለሁ? እንዴት ለማምለጥ እችላለሁ? እንዲህ አይነት ሐሳብ ሲኖርህ ክርስቶስ ቀድሞውኑ እየጮኸ ነው፣ ምክንያቱም እምነትህ ይጮሃል። እንደዚህ በሚጮህ ድምፅ ውስጥ፣ እንደገና የመነሳት ተስፋ ወደ ብርሃን ይወጣል። እንዲህ ዓይነት እምነት ባለበት ክርስቶስም ይኖራል። ምክንያቱም በእኛ ውስጥ እምነት ካለ ክርስቶስም በእኛ ውስጥ ይገኛል” (AUGUSTINE 354-430)
“ወንጌላዊው ለምን ስለዋሻው ልዩ ጥቁማ አደረገ? በእርግጥ የዲያቢሎስ ዝርፍያ የሰውን ልጅ ያሳለፈበት ዋሻ ነው። የሞት ስግብግብነት የእግዚአብሔርን የእጁ ሥራ ያሰረበት ዋሻ ነው። ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር፥ በኃይለኛ ሞት ላይ ኃይለኛ በር ተገጥሞበት ነበር። ክርስትያኖች ሆይ፣ ስለ ኃጢአታችን እናልቅስ፣ እንዲሁም ለማይሰሙት ሙታን ከሚያለቅሱት ከአረማውያን ጋር አናልቅስ” (PETER CHRYSOLOGUS 380-450)
ቁ39 “ኢየሱስ፥ ድንጋዩን አንሡ አለ። የሞተውም እኅት ማርታ፥ ጌታ ሆይ፣ ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል አለችው”፥ …
“ኢየሱስ ገና በቤት ውስጥ በሞት ተኝታ የነበረች የምኩራብን አለቃ ሴት ልጅ አስነስቷል። ከከተማይቱ በሮች ውጭ እየተወሰደ የነበረውን የመበለቲቱ ወጣት ልጅ አስነስቷል። በመጨረሻም ለአራት ቀን በመቃብር ውስጥ የነበረውን አልዓዛር አስነስቷል። ስለዚህ እያንዳንዱ ለገዛ ነፍሱ ትኩረት ይስጥ። ኃጢአትን በመሥራት ነፍስ ትሞታለች፣ ኃጢአት የነፍስ ሞት ነው። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ኃጢአት የሚከናወነው በሐሳብ ብቻ ነው። የአእምሮ እሺታ ገድሎሃል፣ ነገር ግን እንዲህ አይነት ሞት ውስጣዊ ብቻ ነው፣ ምክንያቱም እርኩስ ሐሳቡ ገና ወደ ተግባር አልተለወጠም። ስለዚህ ገና ከቤት ወደ መቃበር ያለተወሰደች ሴት ልጅ ከአእምሮ ወደ ድርጊት ያላለፈ ኃጢአት ምሳሌ ናት። ኢየሱስ አድኖአታል። ነገር ግን በውስጥህ በክፉ ነገር ተደስተህ ክፉን ነገር በድርጊት ከፈጸምክ፣ እንደ መበለቲቱ ወጥተህ ሬሳውን ከከተማ በር ውጭ ተሸክመህ ወደ መቃብር እየሄድክ ነው ማለት ነው። አሁንም ጌታ ኢየሱስ የመበለቲቱን ወጣት ልጅ አድኖአል። ኃጢአት ብትሠራም ንስሐ ግባ፣ ጌታም ያስነሳሃል እና ወደ እናትህ ቤተክርስቲያን ይመልስሃል። ሦስተኛው የሞት ምሳሌ አልዓዛር ሞት ነው። እሱ ከኃጢአት ልማድ የሚመጣ አሰቃቂ ሞት ነው። ምክንያቱም የኃጢአት ልማድ በኃጢአት ከመውደቅ ይብሳል። ኃጢአት መሥራት የለመደ፣ እንደ ግማት የሚያስጠላ ህይወቱ የተበላሸ ነው። ሆኖም የክርስቶስ ስልጣን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለውን ሰው ወደ ሕይወት መመለስ ችሏል” (AUGUSTINE 354-430)
ቁ41 “ድንጋዩንም አነሡት። ኢየሱስም ዓይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ፥ አባት ሆይ፣ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ”፥ …
“ድንጋዩን ከመቃብሩ አፍ አስነሱት። የበሰበሰውን የአልዓዛርን ሽታ ስለመሰከረ፣ ሕዝብ ሁሉ ተደንቆ ነበር። ነገር ግን በህይወት የተሞላ እስትንፋስ፣ በመልካም መዓዛ የተሞላ አፍ፣ ሞትን የሚያስፈራ አንደበት፣ በትእዛዙ ኃያል የሆነው ፈጣሪ፣ ላዘኑት ደስታ፣ ለወደቁት መነሻ፣ ለሙታን ትንሳኤ፣ የኃያላን ጉባኤ እና ተስፋ ለቆረጡት ተስፋ በመሆን፣ ኢየሱስ በመካከላቸው ገባ” (ATHANASIUS 297-373)
ቁ43 “ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ፥ አልዓዛር ሆይ፣ ወደ ውጭ ና ብሎ ጮኸ”፥ …
“በስሙ አልዓዛርን ባይጠራ ኖሮ የኢየሱስ ታላቅ ኃይል በመቃብር የነበሩትን ሁሉ ያስነሳ ነበር” (MAXIMINUS 365)
“ወደ ውጭ ና። እነሆ፣ በአንተ አጠገብ ቆሜአለሁ። እኔ ያንተ አምላክ ነኝ፣ አንተ የእጆቼ ሥራ ነህ። በመጀመሪያ እኔ ራሴ አዳምን ከአፈር ሠራሁ እና እስትንፋስን ሰጠሁት፥ እስትንፋስስ እሰጥህ ዘንድ አፍህን ክፈት። በእግሮችህ ላይ ቆመህ ጥንካሬን ተቀበል፥ እኔ የፍጥረት ሁሉ ጥንካሬ ነኝና። እኔ ቀጥ ያለ ብትር ነኝ፥ መጥፎ ሽታ ከአንተ እንዲለይ አዝዣለሁ። እኔ ከገነት ዛፎች ጣፋጭ ሽታ ነኝና። እነሆ፣ የኢሳይያስ ትንቢት በአንተ ውስጥ ይፈጸማል፥ ልዑል እግዚአብሔር የሞትን ኃይል ለዘለዓለም ያጠፋል፣ ከሰዎች ፊት ሁሉ እንባን ያብሳል” (ATHANASIUS 297-373)
Leave a reply