የአብይ ጾም 4ኛ እሁድ (A LENT-4)

የአብይ ጾም 4ኛ እሁድ (A LENT-4)

ወንገል፥ ዮሐንስ 9፥1-41

ቁ7 “ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ አለው”፥ …

“እግዚአብሔርም ደግሞ ተናገረኝ እንዲህም አለኝ፥ ይህ ሕዝብ በጸጥታ የሚሄደውን የሰሊሆምን ምንጭ ውኃ ጠልቶአልና…” ብርቱና ብዙ ውኃ ባለው በኤፍራጥስ ወንዝ ተደስተዋል (ትንቢተ ኢሳይያስ 8፥5-7)። “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም። በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፤ በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል” (መዝሙረ ዳዊት 23)። እምነት በጸጥታ በሚሄድ ውኃ ውስጥ፣ በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይገኛል። እንቁም፣ ፀሎትን እንጨምር፣ ወደ ራሳችን እንግባ። እግዚአብሔር የሚገኘው በጸጥታ በሚፈስ ውሃ ውስጥ ነው እንጂ በኤፍራጥስ ወንዝ ብርቱ ግፊት ውስጥ አይገኝም።

1ኛ ንባብ፥ 1ኛ ሳሙኤል 16፥1-13

ሳሙኤል ዳዊትን ይቀባል፣ ከዚህ ቀን ጀምሮ ዳዊት ንጉሥ ነው። ነገር ግን ዳዊት እንደ ንጉሥ የሚገለጸው ከሳኦል ሞት በኋላ ብዙ ችግርና መከራ ካሸነፈ በኋላ ብቻ ነው። ሆኖም ግን ከዚያ በፊት እግዚአብሔር አስቀድሞ በስውር መርጦት ነበረ።

ማንም እንደማያስተውለው እግዚአብሔር በስውር ይሠራል። አዲስ ንጉሥ ቀድሞውኑ እዚያ ነበር፣ ግን ይህ ንጉሥ ለብዙ አመታት ሳኦል በከባድ ድብርት ውስጥ ወድቆ በነበረበት ጊዜ የሳኦልን ብስጭት ለማረጋጋት በገናን ብቻ ይጫወት ነበር። በእግዚአብሔር የተቀባ ንጉሥ ለጊዜው በገናን ብቻ ይጫታል። ሕዝብም ንጉሥ መሆኑን አያውቅም።

እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር በስውር ይሠራል። የእግዚአብሔር እቅድ የሚከናወነው በዝምታና በትህትና ነው። እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች በትህትናና በጸጥታ ያሳድጋቸዋል፣ ይህ የእግዚአብሔር እቅድ ይበልጥ ውጤታማ ይሆናል። ኢየሱስም እንዲሁ ሠላሳ ዓመት በናዝሬት ኖሮአል! በዚህ ሠላሳ ዓመት ጊዜ እግዚአብሔር የጠፋ ይመስላል፣ በሕዝቡ ላይ ግድ የለሽ የሆነ ይመስላል፥ እርሱ ግን መጣ፣ ሰው ሆነ፣ ወንድማችንም ሆነ። ሆኖም ግን ከሁሉ የሰው አይን ተደብቆ በናዝሬት ውስጥ እያደገ መጣ።

ከእግዚአብሄር ጋር ችኮላ አያስፈልግም። የእግዚአብሄርን ዝምታ ለመቻል ትዕግስት ያስፈልጋል፣ ዝም ቢልም እንኳን በእግዚአብሔር መተማመን አለብን። በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ብዙን ጊዜ እግዚአብሔር የሌለ ይመስላል፣ ብቸኝነትና ሁሉም ነገር ጥቅም እንደሌለው ይመስላል፣ ሕይወታችን ወደ ባዶነት እንደገባ ሆኖ ይሰማናል።

ዳዊት ጉልበት ስላልነበረው፣ እንደ ሳኦል ያን ያህል ቁመቱ ረጅም ስላልነበረ እና ገና ልጅ ስለነበረ፣ አባቱ ራሱ ከርሻ አላስጠራውም። በእግዚአብሔር የተመረጠ ሊሆን አይችልም ብሎ ያስብ ነበር። የበግ እረኛ ሆኖ መቅረት ነበረበት ብሎ ያስብ ነበር።

ቢሆንም ግን እግዚአብሔር የተሰጣቸው ሥራ ለመሥራት ብቃት ያላቸው የማይመስሉትን ሰዎች ይመርጣል።

Leave a reply