የአብይ ጾም 3ኛ እሁድ (A LENT-3)

የአብይ ጾም 3ኛ እሁድ (A LENT-3)

ወንገል፥ ዮሐንስ 4፥5-42

ቁ6 “በዚያም የያዕቆብ የውሃ ጕድጓድ ነበረ። ኢየሱስም መንገድ ከመሄድ የተነሳ ስለደከመው በጕድጓድ አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ስድስት ሰዓት ገደማ ነበረ”፥ …

እዚህ ላይ ሁለት ነገሮች ይጠቁማሉ፥ ድካምና ስድስተኛ ሰዓት። ስድስተኛ ሰዓት ክርስቶስ የተሰቀለበት ሰዓት ነው፣ ድካም ደግሞ የመስቀሉ ድካም ነው። በሰማርያ ጕድጓድና በመስቀል ላይ የተከሰተውን ማነጻጸር እንችላለን፥ በሰማርያ ጕድጓድ ኢየሱስ ውሃን ይጠይቃል፣ በመስቀል ላይ “ጠማኝ” ይላል። በሰማርያ ጕድጓድ ኢየሱስ የውሃን ጥማት ለዘላለም የሚያረካ የሕይወትን ውሃ ይሰጣል፣ በመስቀል ላይ ጎኑ ራሱ የሕይወት ውሃ ምንጭ ይሆናል።

“ለሁሉ ሰው የሕይወት እስትንፋስ ምንጭ  የሆነው ክርስቶስ በጉዞ ምክንያት ደክሞ ስለነበረ በሰማርያ የውሃ ምንጭ አጠገብ ተቀመጠ። ጊዜውም የሚያቃጥል ሙቀት ውቅት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ጊዜው ስድስት ሰዓት ገደማ ነበረ። መሲሑ በጨለማ ያሉትን ሊያበራላቸው የመጣው እኩለ ቀን ነበር። ውሃን የፈጠረ ለመጠጣት ሳይሆን ለማንጻት ወደምንጩ መጣ። የዘላለማዊነት ምንጭ ችግረኛ መስሎ በሴት ሐዘን ውሃ አጠገብ ነበረ። ሳይደክመው በባሕር ላይ የተራመደ፣ የዘላለማዊ ደስታና ደህንነት ምንጭ የነበረ፣ ከጉዞ የተነሳ ደክሞታል” (ROMANUS MELODUS 536-556)

ቁ8 “ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበርና”፥ …

ደቀመዛሙርት ወደ ከተማ ከሄዱ በኋላ ትዕይንቱ በግል ይከናወናል። በዚሁ ጕድጓድ አጠገብ የሁለት ምኞቶች ብቸኝነት የገናኛል። ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት የምንችለው ለየግል ብቻ ነው፥ ሌላ ሰው በእኔ ፋንታ ከእግዚአብሔር ጋር ሊገናኝ አይችልም። ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት የምንችለው ልብ በልብ ብቻ ነው።

ቁ10 “ኢየሱስ መልሶ፥ የእግዚአብሔርን ስጦታና ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ ኖሮ፣ አንቺ ትለምኚው ነበር፣ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር አላት”፥ …

የማታውቂ ስጦታ የህይወት ስጦታ አለ። ፍቅርን ለማገኘት መጣሽ፣ ደስታን ለማገኘት መጣሽ፣ ነገር ግን የዚህ ፍቅርና ደስታ ውሃ ከየት እንደሚመነጭ አታውቂም።

ሰው ሁሉ የተጠማ ነው፣ ግን ጥማቱን የሚያረካ ውሃ አያገኝም። ስለዚህ፥ ‘የእግዚአብሔርን ስጦታ ብታውቂ!’… የማታውቂ ስጦታ አብ ለወልድ፣ ወልድ ደግሞ ለአብ ያለው የእግዚአብሔር ፍጹም ፍቅር ነው፣ በእኛና በእናንተ መካከል ያለው ፍቅር ነው። ታላቁ ስጦታ ይህ ነው! ወልድ የአብን ህይወት ራሱ ሊያመጣልን መጣ። ይህንን ብታውቂ አንቺ ትጠይቂኝ ነበር እናም ሕይወት የሚሰጥ ውሃ እሰጥሽ ነበር። ብዙ አይነት ውሃ አለ። ረግቶ የሚቆይ የሞተ ውሃ አለ፣ የሚፍለቀለቅ ህያው ውሃ አለ፣ ሁሉን የሚያጠፋ ጨዋማ ውሃም አለ እና ከውኃም የበለጠ ትልቀት ያለው ነገር አለ፥ በመንፈስና በፍቅር የሚንቀሳቀስ ውሃ አለ፣ በፍቅር የሚንቀሳቀስ ህይወት አለ፥ ደስታን የሚሰጥ ይህ ነው። እስካሁን ድረስ ፈልገሽ ያጣሹን ውሃ ልሰጥሽ እፈልጋለሁ።

“የሕይወት ውኃ በፍጥነት የሚፈስ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው፣ ምክንያቱም በዲያብሎስ ወንጀሎች ምክንያት ደረቅና መካን የሆነ የሰው ተፈጥሮ እስከሥሮቹ ተጠምቶአል። አሁን ግን የሰው ተፈጥሮ ወደ ቀድሞ ውበቱ ተመልሷል፣ ሕይወት በሚሰጠውም በመጠጣት በተለያየ የውበት አይነት ውብ ተደርጎአል። ጥሩ የሕይወት ፍሬ እየሰጠ፣ ወደ እግዚአብሔር የፍቅርን ጤናማ ቡቃያ ያሳድጋል” (CYRIL OF ALEXANDRIA 375-444)

ቁ11 “ሴቲዮዋም፥ ጌታ ሆይ፥ መቅጃ የለህም ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ ታድያ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ?”፥ …

“ይህ የውሃ ጉድጓድ ከህያው ምንጭ የሚመነጭ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ነው። መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ የዘላለም ሕይወት ምንጭ ነው… ይህ ውሃ እንዴት የሚያድስ ነው!” (AMBROSE 333-397)

ቁ13-14 “ኢየሱስም መልሶ፥ ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ ምክንያቱም እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት”፥ …

እግዚአብሔር ለአዳም የተናገረው የመጀመሪያው ቃል ‘የት ነህ?’ የሚል ነበረ። አዳም ከቦታው ወጥቶ ነበረ፥ የሰው ልጅ ቦታ እግዚአብሔር ነው። በዚህ ቦታ እያለሁ፣ ቤት እኖራለሁ፣ ከሌሎች ጋር እና ከራሴ ጋር ከአጽናፈ ሰማይም ጋር በሰላም እኖራለሁ። ከማንም የማልለምነው ደስታ ከውስጥ የሚፈልቅ ውሃ ይህ ነው። የተሰጠኝ ውሃ የሚገዛ አይደለም፥ የመንፈስ ስጦታ ነው፣ ይህ ስጦታ እግዚአብሔር በውስጤ እንዲኖርና እንደርሱ እንድሆን የሚያደርግ ፍቅር ነው።

እረፍት የማያገኝ ጥማት የሰው ዘር ዋና መለያ ነው። ጥማት ምኞት ነው፣ ሰው ምኞት ነው። ምንም እንኳን መላውን ዓለም ቢያገኝም፣ ሰው ከዚያ በላይ ይፈልጋል። ሰው ወሰን የሌለውን ለመያዝ የሚመኝ የሚይዝ ማለቂያ የሌለው የውሃ ጎድጓድ ነው።

ቁ15 “ሴቲዮዋም፥ ጌታ ሆይ፥ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳልጠማና ውኃም ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ ይህን ውኃ ስጠኝ አለችው”፥ …

ኢየሱስ ‘ውሃ ስጪኝ’ ይላል፤ ሳምራዊቷ ሴት ‘ውሃ ስጠኝ’ ትላለች። በአንድ በኩል ኢየሱስ የሰው ልጅ የማዳን ጥማት አለው፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሴቲቱም የመዳን ምኞት እየተነቃም ይሄዳል፥ ‘ከዚህ ውሃ ስጠኝ! ሌሎች ውሃዎችን አውቃለሁ፣ የውሃን ጉድጓድ አውቃለሁ፣ ውሃን የመሳብ ልፋት አውቃለሁ፣ አንተ የምትለኝ ውሃ ግን እስካሁን አላገኘሁም፣ ስጠኝ’። እዚህ ላይ በመጨረሻ የኢየሱስ ጥማትና የሴቲቱ ጥማት አንድ ሆኗል።

ቁ16 “ኢየሱስም፥ ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ተመለሺ አላት”፥ …

ኢየሱስና ሰቲዮዋ ስለ ውሃ እያወሩ ነበር። ባለቤቷ ከቅሃ ጋር ምን ግንኙነት አለው? የማይገናኝ ይመስላል ግን ይገናኛል፣ ምክንያቱም ውሃ የሕይወት ምንጭ ከሆነና ፍቅር ደግሞ የደስታ ምንጭ ከሆነ፣ ባለቤቷ የፍቅሯ ምንጭ መሆን ነበረበት። ስለዚህ ‘ሂጂና ባልሽን ጥሪ!’ ከተባለች በኋላ ‘ባል የለኝም’ ትላለች። ይህች ሴት ምንም እንኳን ስድስት ባሎች የነበሩአት ብትሆንም፣ ማንም ባል እንደሌላት ተገንዝባለች፣ ምክንያቱም አንዳቸውም እርስዋ የፈለገችውን የፍቅርና የህይወት ምኞት ሊያረኩ አልቻሉም።

ቁ17-18 “ሴቲዮዋም መልሳ፥ ባል የለኝም አለችው። ኢየሱስ፥ ባል የለኝም በማለትሽ መልካም ተናገርሽ። ምክንያቱም አምስት ባሎች ነበሩሽና፥ አሁን ከአንቺ ጋር ያለው ባልሽ አይደለም፤ ስለዚህ እውነት ተናግርሻል አላት”፥ …

እኛ ከፈለግናቸው ነገሮች አንድም ነገር ጥማታችንን ያረካ የለም፣ ስለዚህ በጥልቃችን ያለው እውነት ይህ ነው፥ ጥማታችን እረፍት የሌለው ነው፣ የምንፈልገውን ውሃ ገና አላገኘንም። ነገር ግን ጥማታችን ታላቅነታችን ነው፥ ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ነፃ ማውጣት የፈለገው ይህ ነው።

የመጀመርያ ባል ምግብ ሲሆን፣ ሁለተኛ ባል ደግሞ ወሲብ ነው። ሦስተኛ ባል እወቀት ሲሆን፣  አራተኛ ባል ስነጥበብ ነው። አምስተኛው ባል ጭንቀት ነው፣ ምክንያቱም ምግብ፣ ወሲብ፣ ዕውቀትና  ስነጥበብ፣ ያለ እግዚአብሔር ፍቃድ፣ እኛ የምንፈልገውን ነገር ሊሰጡን አይችሉም። ይህ አምስተኛ ባል ደግሞ ክብር ያለው ባል ነው፣ ምክንያቱም ወደ ስድስተኛው ባል የሚመራን በመሆኑ ነው።

ስድስት ቁጥር የሰው መለያ ቁጥር ነው። ስለዚህ ስድስተኛ ባል ማለት ሰው መሆን ማለት ነው። የዚህ አለም ነገሮች መሙሉ ብታገኝም (ከአንደኛ እስከ አራተኛ ባል)፣ የሚሰማህ ጭንቀትና ቅሬታ (አምስተኛ ባል) ልብህ ከነዚህ ነገሮች በላይ ላለው ጥማት እንደተፈጠረ ትገነዘባለህ (ስድስተኛ ባል)፤ ስለሆነም ‘እውነትን ተናግረሻል!’

ሴቲቱ ከስድስተኛው ባሏ ጋር መኖር ተለማመደች። ስድስተኛ ባል የጉድጓዱ ውሃ ነው። የጉድጓዱ ውሃ ደግሞ ሰው በተፈጠረበት በስድስተኛ ቀን የተሰጠ የህይወት ሕግ ነው። ሕግ ግን አይበቃም። ህግ ፍቅርና ህይወት አይደለም፥ ሰው መሆን አይበቃም።

ሴቲዮዋም ውኃን ለመቅዳት ወደ ጉድጓድ መጣች፣ ስለሆነም ኢየሱስ ‘ምንም ባል የለሽም፣ የነበሩሽ አምስቶቹ ባሎች፣ አሁንም ያለሽ ባል ጨምሮ (የሥርዓታማ ሕይወት ሕግ፣ በልፋት የሚቀዳ የጉድጓድ ውሃ) ባልሽ አይደለም’።

እዚህ ላይ እንደምንገነዘበው፣  በእነዚህ ስድስት ባሎች አማካይነት ደረጃ በደረጃ የደስታን ፍለጋ ታሪካችንን ማየት እንችላለን።

ከዚህ ሁሉ በኋላ የኢየሱስ ጥማት ማወቅ እንችላለን፥ የኢየሱስ ጥማት በአብ የተላከውን ነብይ የሚቀበልና የሰውን ጥማት የሚያረካውን ሰባተኛ ባል ለሴቲቱ የመስጠት ጥማት ነው።

ነብይ ለሰው ልጅ እውነትን የሚናገርና በሰው ልብ ያለውን ምኞት የሚያሳይ መልእክተኛ ነው። እኛም ምኞታችንን መርምረን ከሴቲቱ ጋር ተመሳሳይ ጉዞ መፈጸም እንችላለን።

ቁ19-20 “ሴቲዮዋም፥ ጌታ ሆይ፥ አንተ ነቢይ እንደሆንህ አሁን አወቅሁ። አባቶቻችን በዚህ ተራራ ላይ ሰገዱ፤ እናንተ ግን፥ ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው”፥ …

አሁን ሴቲቱ ኢየሱስ ነቢይ መሆኑን ተገነዘበች። እዚህ ላይ እርሷ ወደ መንፈሳዊ ደረጃ ስላለፈች ‘የት ይሰገዳል’ ብላ ትጠይቃለች። ሰው የፍጽምና ጥማት እንደሆነ፣ ለፍጹም ፍቅርና ለእግዚአብሔር ብቻ እንደሚጠማው ተረድታለች። ስለዚህ ስለ ስግደት ጉዳይ ታነሳለች።

ቁ21-22 “ኢየሱስም እንዲህ አላት፥ አንቺ ሴት፥ እመኚኝ”፥ …

የሰመርያ ሴት ሰበናተኛ ባለቤቷን አገኘች።

ቁ23 “ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብም የሚፈልገው በዚህ መንገድ የሚሰግዱለትን ነው”፥ …

የአምልኮ ስፍራ አብንና የአብን ፍቅር የሚያውቅ የሰው ልብ ነው።

“የሰማርያ ሴት መለኮታዊ ምስጢሮችን ተማረች፥ እግዚአብሔር መንፈስ እንደሆነና በአንድ ቦታ ሳይሆን በመንፈስ እንደሚሰገድ ተማረች። በተጨማሪም ክርስቶስ መሲሕ መሆኑን ተማረች። የቤተክርስቲያንን ውበት የምትገልፅ ይህች ሴት ይህን በሰማች ጊዜ የሕጉን ምስጢር ተምራ አመነች” (AMBROSE 333-397)

ቁ24 “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባቸዋል”፥ …

“እውነተኛ አማኝ እግዚአብርሔርን በፅድቅና የሚያከብርና የትም ቦታ መያዝ ከማይቻል አምላክ ጋር መነጋገር እንደሚችል በንጹህ ህሊና የሚያምን ነው” (THEODORE OF MOPSUESTIA 350-428)

“መጸለይ የሚመኝ፣ ለሚጸልይ ጸሎትን የሚሰጥ እግዚአብሔር ያስፈልገዋል። ስለዚህ ስምህ ይቀደስ መንግሥትህ ይምጣ በማለት ለምነው፥ ይህም መንፈስ ቅዱስና የአብ አንድ ልጁ ነው። አብን በመንፈስና በእውነት አምልኩ በማለት ይህን ማስተማር ፈልጎአል። እግዚአብሔር ፈላጊ ከሆንክ፣ በእውነት ትጸልያለህ። በእውነት ከጸለይህ፣ እግዚአብሔርን ፈላጊ ትሆናለህ” (EVAGRIUS OF PONTUS 345-399)

“እግዚአብሔር በከፍተኛ ቦታ ላይ ይኖራልና ወደርሱ ቀርቤ ሊሰማኝ እንዲችል የምጸልይበትን ከፍተኛና ተደራሽ ያልሆነውን ተራራ እንዴት እመኛለሁ በማለት ትጮሃለህ። አዎን፣ እግዚአብሔር ከፍ ባለ ቦታ ላይ ይኖራል፣ ግን እሱ ደግሞ ትሑቶችን ይመለከታል… ወደ እሱ መቅረብ ከፈለክ ውረድ። ወደ ላይ መውጣት ትፈልጋለህን? ወደ ላይ ውጣ፣ ግን ተራራ አያስፈልግም። ወደ ላይ የሚመራ ጉዞ በልብና  በእምባ ሸለቆ ውስጥ እንደሚገኝ ተጽፎአል (መዝሙረ ዳዊት 84፥6)። ዝቅተኛ ቦታ ስለሆነ፣ ሸለቆ ትህትናን ያመለክታል። ስለዚህ ሁሉንም ነገር በውስጥህ አድርግ። ምንም እንኳን ከፍ ያለና የተቀደሰ ቦታ ብትፈልግም፣ ራስህን የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ አድርግ። በቤተመቅደስ ውስጥ መጸለይ ትፈልጋለህን? በውስጥህ ጸልይ። በመጀመሪያ ግን የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ሁን፣ ምክንያቱም እርሱ በራሱ ቤተመቅደስ ገብቶ የሚለምነውን ይሰማል” (AUGUSTINE 354-430)

ቁ26 “ኢየሱስም፥ እንሆ አሁን የማነጋግርሽ እኔ እርሱ ነኝ አላት”፥ …

በማስተዋል ከተነበበ ‘እኔ ነኝ’ ለሙሴ ራሱን የገለጠ የእግዚአብሔር ስም ነው። እና ‘የማነጋግርሽ እኔ ነኝ!’ በሚል ቃል ውስጥ ከዚህ የበለጠ ምስጢራዊ ነገር አለ፥ ይህ በጣም አስደሳች የእግዚአብሔር መግለጫ ነው። እግዚአብሔር ማን ነው? ይህችን ሴት እንደሚያነጋግራት አንተንም የሚያነጋግር ነው። እግዚአብሔር ቃል ነው፣ ግንኙነትና ኅብረት ነው፣ ራሱን መስጠት ነው፣ ቅርርብና ውይይት ነው። እግዚአብሔርን የምታውቀው በዚህ ጓደኛ ከጓደኛ ባለው ውይይት ውስጥ ነው።

“ቀስ በቀስ፣ ኢየሱስ እሷን ወደከፍተኛ ደረጃ መራት። እርሷ በመጀመሪያ ውሃ የጠማውን ሰው አየች፤ ከዚያ በኋላ ከአይሁድ ክፍለአገር የመጣ ሰው መሆኑን አወቀች፤ ቀጥሎ ነቢይን አየችና በመጨረሻ እግዚአብሔርን አየች። ውሃ ስለጠማው አሳመነችው፤ ከአይሁድ ክፍለአገር ስልነበረ ከርሱ ራቀች፤ መምህር ስልነበረ ጠየቀችው፤ ነብይ ስልነበረ ተነበበች፤ መሲሕን ስላገኘች ሰገደችለት (EPHREM THE SYRIAN 306-373)

ቁ28 “ከዚህ በኋላ ሴቲዮዋም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ሄደች”፥ …

“የማነጋግርሽ እኔ እርሱ ነኝ የሚል ቃል በመስማት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በልቧ ውስጥ በመቀበል፣ እንስራዋን ትታ ወንጌልን ፈጥና ከመስበክ ውጭ ሌላ ምን ልታደርግ ትችላለች? ምኞቷን ጣለችና ወንጌልን ለመስበክ ሮጠች። ወንጌልን የሚሰብኩ ሁሉ ይማሩ፥ በውሃ ጉድጓድ አጠገብ እንስራቸውን ይጣሉ። እንስራዋን ጥላ ክርስቶስ እንዲታወቅ ለማድረግ ወደ ከተማ ትሮጣለች” (AUGUSTINE 354-430)

“ውሃን እንደሚስብ ስፖንጅ፣ ህይወትን እየተሸከመች ከጉድጓዱ ተለየች፥ ወሰን የሌለውን ደስታና ስርየት በማሳወቅ የእግዚአብሔር ተሸካሚ ሆነች” (ROMANUS MELODUS 536-556)

ቁ29 “ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ ምናልባት እርሱ መሲህ ይሆንን? አለች”፥ …

“ሐዋርያት በተጠሩ ጊዜ መረባቸውን እንደተዉ፣ ሴቲዮዋም የወንጌልን ሥራ ለመሥራት የውሃ መቅጃ እንስራዋ ትተዋለች። እንድርያስና ፊልጶስ እንዳደረጉ አንድ ወይም ሁለት ሰዎችን ብቻ ሳይሆን፣ የከተማ ነዋሪዎች በሙሉ ትጋብዛለች” (JOHN CHRYSOSTOM 344-407)

እግዚአብሔር ፍቅር ከሌለው ‘ፃዲቅ’ ይልቅ፣ አፍቃሪ ኃጢአተኛን ይመርጣል። ፍቅርን ማሠልጠን ይቻላል፣ ነገር ግን ትዕቢት አይቻልም። አውቃለሁ ብሎ የሚያስብ ሰው አብዛኛውን ጊዜ እውነትን አያገኝም። እንደ ሰምራዊት ሴት ደስታ የሌለው ኃጢአተኛ መሆኑን የሚያውቅ ሰው ከሚመስለው በላይ ለሰላም፣ ለደስታና ለድህንነት ቅርብ ነው።

ቁ40-41 “የሰማርያ አገር ሰዎችም ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ በእነርሱ ዘንድ እንዲኖር ለመኑት፤ በዚያም ሁለት ቀን ያህል ኖረ። በቃሉም ምክንያት ሌሎች ብዙ ሰዎች በእርሱ አመኑ”፥ …

ታዲያ እምነት ምንድነው? እምነት የሰማርያ ሴት ያደረገችውን ተመሳሳይ ጉዞ መፈጸም ነው። እምነት እውር ናት ይባላል፣ እምነት ግን እውር አይደለችም። እምነት ምክንያታዊ ጥያቄ ነው፣ የውሃና የምግብ ጥያቄ ነው፣ የፍቅርና የመንፈሳዊ ትዳር ጥያቄ ነው፣ የአምልኮ ስፍራ ነው፣ የመዝራትና የመከር ጊዜ ነው። ሰው በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ስለሚኖር፣ እምነት በጣም ምክንያታዊ ጥያቄ ነው። እምነት ከማረጋገጫ አያመልጥም። እንደ ስድስቱ ባሎች ከማረጋገጫ ያሚያመልጡ ጣዖቶች ናቸው እንጂ ሰባተኛው ባል ከማረጋገጫ አያመልጥም (“ሴቲዮዋንም፥ አሁን የምናምን ስለ ቃልሽ አይደለም፥ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን ይሉአት ነበር”)።

በመጨረሻ፣ በእምነት አማካይነት ከኛ ጋር እንዲኖር ክርስቶስን እንለምነዋለን፤  እኛም ከርሱ ጋር እንድንኖር ክርስቶስ ይለምነናል።

Leave a reply