የአብይ ጾም 2ኛ እሁድ (A LENT-2)

የአብይ ጾም 2ኛ እሁድ (A LENT-2)

ወንገል፥ ማቴዎስ 17፥1-9

ቁ1 “ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው”፥ …

“ከስድስት ቀንም በኋላ”፥ … ከባርነት ነፃ ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት ለመድረስ እስከ ዛሬ ድረስ አብሮ በምጥ ጭንቀት ተይዞ በመቃተት ላይ ያለው የፍጥረት ፍጻሜ ሰባተኛው ቀን (ሮሜ 8፥21-22) የሁሉ ፍጥረት አላማ ነው።

“ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ”፥ … “ጴጥሮስ ያዕቆብና ዮሐንስ ከርሱ ጋር ባላቸው ቅርበትና ፍቅር ምክንያት ኢየሱስን ወደ ተራራ ይሸኛሉ” (JOHN CHRYSOSTOM 344-407)

ታቦርና ደብረዘይት ማነፃፀር እንችላለን። በታቦር ላይ አብ ልጁን ሲጠራ፣ በደብረዘይት ላይ ኢየሱስ አባቱን ይጠራል። ታቦር ላይ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን ያሳያል፣ በደብረዘይት ደግሞ ኢየሱስ ሰው መሆኑን ያሳያል።

ቁ2 “በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ”፥ …

ይህ መለወጥ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ሁሉ ያቀደ አላማ ነው። እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ለማየት ተጠርተናል። ብርሃንን እንድንለብስና ብርሃን እንድንሆን ተጠርተናል፥ “ብርሃንሽ መጥቶአልና፥ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ፥ አብሪ” (ኢሳይያስ 60፥1)።

ቁ3 “እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው”፥ …

ሙሴና እልያስ፥ የሕግ አማካይና የነቢያት አባት ከኢየሱሰ ጋር ይነጋገራሉ፥ እንዲሁም ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ይነጋገራሉ። የእግዚአብሔር ቃል የሕግና የነቢያት ፍጻሜ ነው። ሙሴና ኤልያስ ደግሞ ሞትን አልቀመሱም፥ አንዱ በእሳት ሠረገላ ወደ ሰማይ ተወሰደ (2ነገሥት 2፥1…)፣ ሌላው ደግሞ ትውፊት እንደሚል እግዚአብሔር አፉን እየሳመው ወደ ሰማይ ወሰደው። ኢየሱስም በሞት ስልጣን አልተነካም።

ቁ4 “ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን። ጌታ ሆይ፥ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ”፥ …

“በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው”፥ … ጴጥሮስ እዚህ መኖር መልካም እንደሆነ ተረድቷል። እግዚአብሔር ዓለምን የፈጠረበት ውበት በልጁ ፊት ላይ ይገለጻል። እዚህ መኖር ጥሩ ነው። ሌላ ቦታ መቀመጥ አስቀያሚ ነውና ልንቆይበት አንችልም። ሰው የእግዚአብሔርን ፊት የሚመኝ ተጓዥ ነው። የእግዚአብሔርን ፊት ብቻ እንደ ቤቱ ቆጥሮ ሊኖርበት ይችላል። ሌላ ቦታ አይመቸውም፥ ከእግዚአብሔር ውጪ ሰው ልክ እንደወለቀ አጥንት ይሆናል።

“በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ”፥ … በሙሴ በኩል የተሰጠው ሕግ በሰዎች መካከል የተተከለ የእግዚአብሔር መጀመሪያ ዳስ ነው። በኤልያስ የተጀመረው ትንቢት በሰዎች መካከል የተተከለ የእግዚአብሔር ሁለተኛ ዳስ ነው። የኢየሱስ ሥጋ በመካከላችን የተተከለ የእግዚአብሔር ሦስተኛ ዳስ ነው።

“ሦስት ዳሶችን አትፈልጉ። የሙሴ ሕግና የነቢያት ቃል የሚፈጸምበትን የወንጌልን ዳስ ብቻ ፈልጉ። በልባችሁ ዳስ ውስጥ የሚሰገደው አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስን አንድ አምላክ ብቻ ፈልጉ” (JEROME 347-420)

ቁ5 “እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፥ እነሆም፥ ከደመናው። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ”፥ …

“ብሩህ ደመና ጋረዳቸው”፥ … ብሩህ ደመና እስራኤልን በበረሓ መካከል የመራው የእግዚአብሔር ምልክት ነው (ዘጸአት 14፥20)፣ የመኖሩም ምልክት ነው (ዘጸአት 24፥15፤ 40፥34፤ 1ነገሥት 8፥10-12)። ራሱን በመግለጥ ራሱን እንደሚሸፍን፣ ራሱን በመሸፈን ራሱን እንደሚገልጽ ሆኖ፣ እጅግ በጣም ከሚያሳውረው ብርሃን ብዛት የተነሳ፣ የእግዚአብሔር መገለጥ ሁልጊዜ የእግዚአብሔር መሸፈን ነው።

“ነፍሴ ሆይ፥ ብሩህ ደመና በጥላው ደቀመዛሙርቱን ጋረዳቸው። ደመናው ብሩህ ከሆነ እንዴት ጥላ ያደርጋል? ደግሞስ ብሩህ ደመና ነው፥ ብሩህ ደመና አይተሽ ታውቂያለሽን? በጭራሽ። ነጭ ቢሆንም ደመና አያንጸባርቅም። ነገር ግን ይህ የእግዚአብሔር ባህርይ ነው፥ እግዚአብሔር ብርሃን ነው ብለሽ ብታስቢ ይደበቃል፣ ጥላ ነው ብለሽ ብታስቢ ብርሃን ሆኖ ራሱን ይገልጻል። እግዚአብሔር “እጅግ በጣም ብሩህ ጭጋግ ነው”

በጥላው የሚሸፍነን ደመና የሚጋብዘን ጥሩ ጥላ ነው እንጂ አስፈሪ ጨለማ አይደለም። በመተማመን የምንጫወትንበት ደመና ነው፥ በማመን ታምኛለሽ፣ በመተማመን ራስሽን በደስታ ትስጪያለሽ። ይህ ማለት እምነት ማለት ነው! እዚህ መኖር መልካም ነው፥ የአብርሃም እምነትና የታቦር ብርሃን ነው”

“እነሆም፥ ከደመናው፥ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ”፥ …

“ነፍሴ ሆይ፥ በዚህ ደመና ውስጥ እንዴት የመንገድ አቅጣጫን ታገኛለሽ? የመንገድ አቅጣጫ የምታገኚ ከደመና በሚወጣ ድምጽ ነው፣ የሚመራሽ ድምፁ ነው (“ከደመናው ድምጽ ወጣ”)። እምነት በደመና ውስጥ እንደቤታችን አድርገን እንድንኖር ያሰለጥነናል፥ “ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው”፣ በደመና ውስጥ ይምትኖሪ ከሆነ አንቺም የምወድሽ ልጄ ነሽ።

የእምነት ሰው በስውር ቦታዎች ውስጥ ሁሉ እየኖረ በገዛ ቤቱ ውስጥ የሚኖር የመስለዋል። እምነት ችቦ ወይም መብራት አይደለም፣ ለማወቅ የምንጠቀምበት መሣሪያ አይደለም (ካወቅሽ እምነት አይባልም)፤ እምነት መንፈሳችን በመተማመን የሚኖርበት ቤት ነው። እምነት ይዘናል እንጂ እኛ እምነትን አንይዝም። ከፍተኛ ነገሮች ሁልጊዜ እንደዚህ ናቸው፥ ከፍ የሚሉ ነገሮች ይይዙናል እንጂ እኛ እንይዛቸውም። ተረድቻለሁ ይዣለሁ የሚባል ከኛ በታች ስላሉ ነገሮች ነው። ተያዝኩ ይዦኛል የሚባል ከኛ በላይ ስላሉ ነገሮች ነው። እምነት የምትኖሪበት መንፈስ ነው፣ አእምሮአችን መድረስ ወደማይችልበት ከፍተኛ ስፍራ ይወስደናል”

ኢየሱስን የሚሰማ ልክ እንደ ፀሐይ እየበራ፣ ፊቱን ወደ መለኮታዊ መልክ ይለውጣል።

ያላዩት ይቅርና ላዩት ደቀመዛሙርቱም እንኳን የታቦርን መለወጥ ለመግለጽ ከባድ ነው። ነገር ግን ሁለት ነገሮች ግልፅ ናቸው፥ የመለወጥ ፍጻሜና መነሻ። ፍጻሜው “ለእኛ እዚህ መኖር መልካም ነው” የሚል መንፈስ ነው፣ መነሻው “አዳምጡት” የሚል ድምጽ ነው። ኢየሱስን የሚሰማ ሁሉ መልካም ፍሬ የሚያፈራ መልካም ዛፍ ይሆናል (7፥18)። ይህ ማዳመጥ ከስጋ ሥራዎች ወደ መንፈስ ፍሬ ያሳልፋል (ገላትያ 5፥19-22)።

ቁ6 “ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ እጅግም ፈርተው ነበር”፥ …  “ለምን ተደናገጡ? ለምን በፊታቸው ወደቁ? የበረሓ ብችኝነት፣ የተራራው ከፍታ፣ ታላቁ ጸጥታ፣ ድንቁ መለወጥ እንዲሁም ንጹህ ብርሃንና የተዘረጋ ደመና ስለነበረ ነው” (JOHN CHRYSOSTOM 344-407)

ቁ7 “ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸውና። ተነሡ አትፍሩም አላቸው”፥ …

ደቀመዛሙርቱ በክብር ሲለወጥ ያዩት ክርስቶስ ወደ እነሱ ቀርቦ ቀሰቀሳቸው። እነርሱ የታያቸው ሕልም አይደለም፣ ከሙታን የሚቀሰቀሳቸው የህይወትና የትንሳኤ ቃል ነው!

ቁ8 “ዓይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም”፥ …

ራሱን የለወጠ፣ መደመጥ ያለበት የተወደደ ልጅ፣ ወደ ኢየሩሳሌም የሚጓዝ እሱን ብቻ ከዛሬ ጀምሮ አይተን እንከትላለን።

1ኛ ንባብ፥ ዘፍጥረት 12፥1-4

በእግዚአብሔርና በሰው ዘር መካከል አዲስ ምእራፍ ይጀምራል። አብርሃም ከቤተሰቡና ከአገሩ ጋር ያለውን ምድራዊ ግንኙነት አቋርጦ፣ በእግዚአብሔር ቃል ብቻ በመተማመን ወዳልታወቀ ምድር መጓዥ አለበትና፣ ምንም እንኳን ሚስቱ ሳራ መሐን ብትሆንም፣ የብዙ ትውልድ አባት እንድሚሆን ያምናል።

እውነተኛውን አምላክ በማያመልኩ ሕዝቦች መካከል፣ የተመረጠውን ሕዝብ አባት ያደርገው ዘንድ እግዚአብሔር አብርሃምን መርጦ፣ በምድር ውስጥ የእግዚአብሔርን ቃል የመጠበቅና የመዳን ተስፋ የማሳወቅ ተልዕኮን ይሰጠዋል።

እንዲሄድ የታዘዘበት አገር የትኛው እንደነበረ አላወቀም፣ ነገር ግን አብርሃም ሁሉንም ትቶ ራሱን ለእግዚአብሔር አስገዛለት። የተገቡ ቃላት የሚፈጸሙት አሁን አይደለም፣ አብርሃም በሩቅ ብቻ ያያቸዋል።

የአብርሃም አመለካከት ከባቢሎን ትዕቢትና ከአዳም አለመታዘዝ ጋር ይቃረናል። የድህንነት መለኮታዊ ዕቅድ የሚጀምረው ከአብርሃም ታዛዥነት ነው፤ ለአብርሃም መታዘዝ ማለት ጉዞ መጀመር ማለት ነው። ይህ ዕቅድ እስከሞት እንኳ በታዘዘ በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ታዛዥነት ይፈጸማል (ፊል 2፥8)። ከአብርሃምና ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ቃል የሚታዘዙ ሰዎች ሁሉ ደግሞ የአብርሃም ልጆች ይሆናሉ፥ “ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ። … እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ” (ገላትያ 3፥6-9)

አብርሃም ወዴት እንደሚሄድ ሳያውቅ ይነሳል። የሰባ አምስት ዓመት ሰው ነበረ፥ የአብርሃም ትክክለኛ እድሜ የተመዘገበ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ለሰው ልጆች አዲስ ዘመን ስለጀመረ ነው።

ለመንፈሳዊ ህይወት፣ ሦስት ጊዜ መነሳት (ከአገር መነሳት፣ ከዘመድ መነሳትና ከአባት ቤት መነሳት) ማለት ከምድራዊ ሰው፣ ከክፋት ዝምድናና በዲያቢሎስ ከተገዛው ዓለም መነሳት ማለት ነው። “የአብርሃም ጥሪና ፍልሰት በመንፈሳዊ ጉዞ የሚሳተፉትን ሁሉ አምሳያ ነው” (ANTHONY THE GREAT 251-356)

“ሐዋረያ ጳውሎስ እንደጻፈ፣ ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆኖአል። ስለዚህ ለአብርሃም የተከሰተ ነገር ለእኛ ተብሎ ከተፃፈ፣ በእምነትና በጽድቅና መንገድ የምንኖር ከሆነ፣ ለአብርሃም የተከሰተው ሁሉ በመንፈሳዊ መልክ በእኛም ላይ እንደሚፈጸም እናያለን። ከአገርህ ከዘመዶችህና ከአባትህ ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ የሚል ትእዛዝ ከእግዚአብሔር ነው፥ በጥምቀት ምስጥር አማካይነት እነዚህ ነገሮች ሁሉ እንደሚፈጸሙ እናምናለን። አገራችን ሥጋችን ናት፥ ሥጋዊ ልምዶቻችንን ትተን የክርስቶስን እርምጃ የምንከተል ከሆነ፣ በትክክል ከአገራችን እንወጣለን። አንድ ሰው ከትዕቢተኛ ትሑት፣ ከሚናደድ ታጋሽ፣ ከራስ ወዳድ ለጋሽ፣ ከቅናተኛ ደግ፣ ከጭካኝ የዋህ መሆን ከቻለ፣ በደስታ አገሩን አለተወምን? በእውነት ወንድሞቼ፣ ከእግዚአብሔር ፍቅር የተነሳ ራሱን እንዲህ መለወጥ የቻለ ሰው በደስታ አገሩን ትቶ የወጣ ነው። አገራችን ሥጋችን ናት። ከጥምቀት በፊት አገራችን የሙታን አገር ነበረች፤ በጥምቀት አማካይነት ግን አገራችን የሕያዋን ምድር ሆነች፥ ሕያዋን በሚኖሩበት ምድር እስካለሁ ድረስ የእግዚአብሔርን በጎነት እንድማይ እተማመናለሁ (መዝሙር 27፥13)። (CAESARIUS OF ARLES 470-543)

Leave a reply