የአብይ ጾም 1ኛ እሁድ (A LENT-1)

የአብይ ጾም 1ኛ እሁድ (A LENT-1)

ወንገል፥ ማቴዎስ 4፥1-11

የኢየሱስ ፈተናዎች ከሦስት ጣዖታት ጋር የተዛመዱ ናቸው፥ እነሱም ድንጋዮችን ወደ እንጀራ የሚቀይር የኢኮኖሚ ጣዖት አምልኮ፤ እግዚአብሔርን መግዛት የሚፈልግ የሃይማኖት ጣዖት አምልኮና ሁሉን ሰው መግዛት የሚፈልግ የፖለቲካ ጣዖት አምልኮ ናቸው።

ቁ1 “ከዚያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው”፥ …

“ይፈተን ዘንድ”፥ … “ልጄ ሆይ፣ እግዚአብሔርን ለማገልገል ራስህን ካቀረብህ ለፈተና ተዘጋጅ” (ሲራክ 2፥1)። ጥሩ ውሳኔ ከተወሰነ በኋላ የመፅናት ትግል አለ። በግሪክ ቋንቋ “ፈተና” “peiro” ይባላል፣ “peiro” ማለት ማቋረጥ ማለት ነው፥ experience በማድረግ (experience = “peiro”), expert (“peiro”) እንሆናለን።

በድሮ ታሪክ ፈተናዎች እንዲሁ ትምህርት ይባሉ ነበር፥ እሱም ልጆች መሆናችንን እንጂ ዳቃሎላዎች አለመሆናችንን የሚያረጋግጠው የልጅ ሕይወት ሥልጠና ነው (ዕብራውያን 12፥8) ፣ በእምነት ደረጃ የመጣራት ሥልጠና ነው (ያቆብ 1፥2-4፣ 1ጴጥሮስ 1፥6)።

“ከዲያብሎስ”፥ … በግሪክ ቋንቋ “ዲያብሎስ” ማለት የሚከፋፍል ማለት ነው፥ እኛን ከእግዚአብሔር በመለየት ብቻችንን የሚተወን ነው። ሰይጣን ደግሞ (በዕብራይስት ቋንቋ “ከሳሹ” ማለት ነው) ተብሎም ይጠራል፥ በምንወድቅበት ጊዜ በኃጢያታችን ላይ አጥብቆ ያለ ምህረት የሚወቅሰን ነው።

ዲያቢሎስ እንዲፈትነው በመፍቀድ፣ ኢየሱስ በፈተናዎቻችን ጊዜ እንዴት መዋጋትና ማሸነፍ እንደምንችል አስተምሮናል፥ ይህም በእግዚአብሔር በመታመን፣ በመለኮታዊ ጸጋና በመንፈሳዊ ጥንካሬ አማካኝነት ነው።

ቁ2 “አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ”፥ … ሙሴ በተራራ ላይ እና ነቢይ ኤልያስ በኦሬብ ተራራ መንገድ ላይ ያሳለፉትን አርባ ቀን ያሳስባል (1ነገሥት 19፥1-8)። ቁጥሩ እስራኤላውያን በበረሓ ውስጥ ያሳለፉትን ዓመታትም ያመለክታል፥ የሰው ሙሉ ህይወት ነው! የሰው ህይወት በረሓ ነው፥ በተጀመረና ገና ባልተፈጸመ መካከል ያለው መካከለኛ መሬት ነው።

ኢየሱስ በምድረበዳ መሰወሩ፣ የሕይወታችንን ማንኛውንም ትልቅ ሥራ ወይንም ውሳኔ ከመጀመራችን በፊት ራሳችንን በጸሎትና በተጋድሎ እንድንዘጋጅ ያስገነዝበናል። በምድረበዳ መሰወር ከመንኛውም ድርጊት በፊት የሚያስፈልግ ዝግጅት ያመለክታል።

ቁ3 “ፈታኝም ቀርቦ። የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው”፥ …

“የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ”፥ … ፈተና የሚያጋጥመው መልካም ህይወት በምትፈልግበት ጊዜ ነው፣ ይህም በሁለት አይነት መንገድ ይከሰታል፥ መልካም ህይወት የመፈጸም ፍላጎትህን በማጥፋት ወይም መልካም ህይወትህን በተሳሳተ መንገድ እንድትፈጽም ነው። የመጀመሪያው አይነት ፈተና “መልካም ህይወት ለእኔ አይሆንም፣ የማይቻል ነው፣ ከባድ ነው፣ አሰልቺ ነው፣ መጥፎ ነው፣ አልችልም” የሚለው በመንፈሳዊ ህይወት ጀማሪ ለሆነው የሚያጋጥመዋል። ሁለተኛው አይነት ፈተና ብዙ መልካም ፍላጎት ቢኖረውም በቂ ማስተዋል ለሌለው በመንፈሳዊ ህይወት ፍጹም ለሆነው ያጋጥመዋል።

መልካም ፍላጎት ላለው ሰው ብዙ ሠርቶ ብዙ ጉዳት እንዲያደርግ፣ ዲያብሎስ ፍላጎቱን እየጨመረበት ማስተዋል ይቀንስበታል። ማስተዋል ላለው ሰው ደግሞ ምንም ነገር እንዳይሠራ ዲያብሎስ ፍላጎቱን ይቀንስበታል።

“ድንጋዮች እንጀራ”፥ … ኢኮኖሚን የግልና ማህበራዊ ህይወት መሰረታዊ መርህ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ጣዖት አምልኮ ነው።

ቁ4 “እርሱም መልሶ። ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው”፥ …

“ተጽፎአል”፥ … ኢየሱስ የሰውን ሃሳብ ትቶ የእግዚአብሄርን አስተሳሰብ ይፈጽማል። የእግዚአብሔር ቃል ፈተናን ለማሸነፍ ብቸኛው መንገድ ነው።

ኢየሱስ ድንጋዮችን ወደ እንጀራ ከመቀየር ይልቅ በአባቱ እንደሚተማመን ማሳየት መርጦአል። ለራሱ ልዩ ጥቅም ብቻ ተአምር አይሠራም፣ ይልቁንም በአባቱ ፍቅር ማደግ ይፈልጋል (የቅድስና መንገድ)።

የጌታችን የመጀመሪያ ፈተና የማህበራዊ ለውጥ አራማጅ መሆን እና ከድንጋይ በቀር ምንም ነገር በማይገኝበት በረሐ ላሉት ሰዎች ምግብ መስጠት ነበር። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ሰዎችን ከእንጀራ የሚበልጥ ነገር ሊመግባቸው እንደሚችል ኢየሱስ ይናገራል።

ሰዎች መመገብ እንዳለባቸው ወይም ማህበራዊ ፍትህ መፈጸም እንዳለበት ኢየሱስ አይክድም። ሆኖም እነዚህ ነገሮች የመጀመርያ አይደሉም። በኢየሱስ አስተሳሰብ እንዲህ አይነት አገልግሎት ለሰማያዊ አባቱ በቂ አይሆንም፥ ምክንያቱም በሰው ልብ ከተፈጨ ስንዴ የሚበልጥ ምኞት አለ፣ እንዲሁም ከሞላ ሆድ የበለጠ ደስታ አለ። ኢየሱስ ለሰይጣን ሲመልስለት እንዲህ እያለ ነው፥ “ፍላጎትን ወደሚያስተናግደው አይነት ሃይማኖት ትፈትነኛለህ፤ ከአዳኝ ይልቅ ዳቦ ጋጋሪ እንድሆን፤ ከመድሐነአለም ይልቅ ማህበራዊ ለውጥ አራማጅ እንድሆን ትፈልጋለህ፣ ከነፍሶች ይልቅ የሰዎችን ሆድ እንድመግብ ትፈልጋለህ። እንጀራ ብቻ ጉዳት ሊሆን ይችላልና ከእግዚአብሔር ቃል በስተቀር እውነተኛ ደህንነት የለም። እንጀራ ብቻ  የምሰጥ ከሆነ፣ ሰው ከእንስሳ አይበልጥምና ቡችላዎችን አስቀድሜ ልጋብዛቸው እችላለሁ። በእኔ የሚያምኑ ሁሉም ሰዎች፣ ቢርባቸውና ቢደክማቸው፣ ቢታሰሩና ቢገረፉም፣ እምነትን አጥብቀው መያዝ አለባቸው። ስለ ሰው ረሀብ አውቃለሁ፥ እኔ ግን ለሆድ ብቻ የሚያስብ ተራ የማህበራዊ ለውጥ አራማጅ ለመሆን አልፈልግም። ለዚህም ነው የጾምኩት፥ እግዚአብሔር ረሀብ ምን እንደሆነ አያውቅም የሚል ማንም እንዳይኖር። ሰዎችን የበለጠ ቅዱስ ሳያደርጋቸው የበለጠ ሀብታም ለማድረግ ቃል የገባውን ማንኛውንም ዕቅድ አልቀበልም”።

ቁ5 “ከዚህ በኋላ ዲያቢሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደውና እርሱን በመቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ”፥ …  ከስጦታዎችን እግዚአብሔር ይልቅ የእግዚአብሔርን ስጦታዎች በመመኘት፣ እግዚአብሔርን መግዛት የሚፈልግ የሃይማኖት ጣዖት አምልኮ ነው። ደግሞ ማረጋገጫን ሁልጊዜ የሚሹ ሁሉ የወላጆቻቸውን ፍቅር በጭራሽ ማወቅ አይችሉም።

ቁ6 “መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው”፥ …

ሁለተኛው ፈተና የትዕቢትና የራስ ወዳድነት ነው። ሰይጣን ለኢየሱስ እንዲህ ብሎ ይጠይቃል፥ “የሰውን ዘር ለማሸነፍ አስደናቂ ተአምር በመፈፀም አቋራጭ መንገድ መውሰድ እየቻልክ፣ ደም የማፍሰስ፣  በመስቀል ላይ የመሰቀል፣  የመናቅና የመዋረድ ረጅምና አድካሚ መንገድ ለምን ትመርጣለህ?።

እንደምንገነዘበው፣ አንዳንድ ጊዜ ዲያብሎስ ራሱን እንደ ምሁር በማድረግ፣ መጽሐፍ ቅዱስን እንደመሰለው ይተረጉመዋል። በዚህ ምክንያት ከቤተክርስቲያን ተውፊት ጋር የማይሰማማ ማንኛውም ትርጓሜ ማስወገድ አለብን።

ቁ7 “ኢየሱስም፥ ጌታ አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል አለው”፥ …

“ጌታ አምላክህን አትፈታተነው፥ … ኢየሱስ የሲና በረሓን ክስተትና የውሃን ፈተና መልሶ ያመጣል (ዘጸዓት 17፥1-7)፥ እምነት የሌላው የማረጋገጫዎች ረሀብ አላው።

ኢየሱስ አስደናቂ ሥራዎችን ቢያደርግ ኖሮ፣ ሰዎች ሁሉ እንዲከትሉት ያደርግ ነበር፤ ነገር ግን ኃጢአት በልባቸው ውስጥ የሚቀር ከሆነ ምን ይጠቅማቸዋል?

ኢየሱስ ለሰይጣን ሲመልስለት እንዲህ እያለ ነው፥ “እኔ ባልረዳቸውም እንኳ በእኔ የሚያምኑትን ሰዎች እፈልጋለሁ፤ ወንድሞቼ የታሰሩበትን የእስር ቤት በር አልከፍትም፤ የሮማ ንጉሥ አንበሶችን አላቆምም፣ ቤተክርስቲያኖቼን የሚደመስሰውን ቀይ መዶሻ አላቆምም፤ እኔ መከራ ውስጥ እንደወደድኳቸው፣ ሚስዮናውያንና ሰማዕታት በእስር ቤትና በሞት እንዲወዱኝ እፈልጋለሁ”።

ቁ9 “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው”፥ … ኢየሱስ ንጉሥ ይሆናል፣ ግን በመስቀል ላይ። እዚያም ለሁሉ ሰው ህይወቱን አሳልፎ በመስጠት ራሱን እንደ ጌታ ይገልጻል።

ቁ10 “ያን ጊዜ ኢየሱስ። ሂድ፥ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው”፥ …

“ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ”፥ … ኢየሱስ የወርቅ ጥጃ ክስተትን መልሶ ያመጣል (ዘጸዓት 32፥1)። ታላቁ፣ የሚያምርና የሚያስፈራ ጣዖት ነው፣ ግን ሁሉ ወርቅ ሆኖ እግሩ ሸክላ ነው (ዳንኤል 2፥31-33)፥ በእግዚአብሔር ድክመት ጠጠር የሚነቀስ ነው።

ኢየሱስ ለሰይጣን ሲመልስለት እንዲህ እያለ ነው፥ “አምልኮን ትፈልጋለህ፣ ነገር ግን አንተን ማምለክ ማለት አንተን ማገልገል ማለት ነውና አንተን ማገልገል ባርነት ነው። በአንተ የተገዙ ዜጎችህ ልትሰጣቸው የማትችለውን ነገር አሁንም ይናፍቃሉ። በመጀመሪያ በሰዎች ልብ ውስጥ ያለውን ክፉ አሸንፋለሁ፣ ከዚያም በኋላ ዓለምን ድል አደርጋለሁ። የማይሞት ነፍሳቸውን ቢያጡ መላውን ዓለም ለማሸነፍ ምንም እንደማይጠቅማቸው እነግራቸዋለሁ። ለጊዜው መንግሥትህን ለራስህ አድርገው። አንድ ነፍስ ከማጣት መንግስታትህን ማጣት ይሻላል። የዓለም መንግሥት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከፍ መደረግ አለበት እንጂ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ አለም መንግሥት መጎተት የለበትም። በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች በግሪካውያንና በሮማውያን ስም በሚስማር ትሰቅለኛለህ፣ ነገር ግን ከሞት እነሳና የምታሸንፍ መስለህ፣ በጠዋቱ ክንፎች ላይ እየተራመድኩ እንድማፈርስህ ታውቃለህ”።

ከኢየሱስ እንማር። በምድራዊ ሕይወቱ የሚገባውን ክብር አልፈለገም፥ እንደ እግዚአብሔር የመቆጠር መብት ቢኖረውም የአገልጋይና የባሪያን መልክ ወስዶአል (ፊሊጵስዩስ 2፥6-7)። በዚህ መንገድ፣ ክብር ሁሉ ለእግዚአብሔር ብቻ እንደሚገባና የወንጌልን አስደናቂ ታላቅነት የግልህን አላማና ፍላጎት መሳሪያ አድርገህ መጠቀም እንድማትችል ትማራለህ።

ቁ11 “ያን ጊዜ ዲያቢሎስ ተወው፥ እነሆም፥ መላእክት ቀርበው ያገለግሉት ነበር”፥ …

በትግል ውስጥ አሸናፊነት የፅናት ውጤት ነው። መጀመርያ ሳያሸንፍ ማንም ሰው የድልን አክሊል አይቀበልም (“እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ” ራእይ 2፥10)። ኢየሱስን ለማገልገል የመጡት መላእክቶች ፈተናዎችን በኃይል ለሚቃወሙ እግዚአብሔር የሚሰጠውን ውስጣዊ ደስታ ያሳዩናል። “በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና” (ያዕቆብ 1፥12)

Leave a reply