የሰብከተገና 1ኛ እሁድ (A ADV-1)

የሰብከተገና 1ኛ እሁድ (A ADV-1)

ወንገል፥ ማቴዎስ 24፥37-44

ቁ37-39 “የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና። በዚያን ዘመን ከጥፋት ውኃ በፊት፥ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፥ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም ነበረ፥ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፥ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል”፥ …

በአጭር ቃላት ጌታችን ሰዎች በመንፈሳዊ ነገሮች ፊት ያላቸውን የግድየለሽነት ሁኔታ ያብራራል። መብላትና መጠጣት፣ ሚስት ወይም ባል ማግባት ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል። በዚህ መንገድ ሲኖሩ ግን ሰዎች ከሁሉ የሚበልጥ ነገር የዘላለም ሕይወት መሆኑን ይረሳሉ። ሰዎች ጥሩ ቢሆንም መጥፎ በንግዳቸው ላይ እያሉ፣ ሁለተኛ የሰው ልጅ መምጣት ባልተጠበቀ ሰዓት ይፈጸማል።

“የክርስቶስ ተቃዋሚ ሲመጣ፣ ራሳቸውን ማዳን ተስፋ መቁረጥን ከለመዱ አመጸኞች መካከል፣ ሕገወጥ ደስታን መፈጸም በጉጉት ይጠብቃሉ። ሆዳምነት መናፈቅና ስካር ይኖራል” (CHRYSOSTOM)

“በመርከቧ ውስጥ ካመለጡት በስተቀር የምድር ፍጥረታት ሁሉ በጥፋት ውኃ ጊዜ እንደጠፉ፣ እንዲሁም በዓለም መጨረሻ መናፍቅነት ይጠፋል፣ ነገር ግን ጻድቃንን ያቀፈውን መርከብ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ብቻ ትድናለች። ከመርከቧ ውጭ የነበረው ነገር ሁሉ ሞተ። እንደዚሁም በዓለም መጨረሻ ከእውነተኛው ቤተክርስቲያን ውጭ የሚገኝ ሁሉ ይጠፋል” (INCOMPLETE WORK ON MATHEW)

“ቃል የሆነ እግዚአብሔር ሲመጣና የዚህን ሕይወት እድገት ሲያበቃ፣ “ለዓይኖቻቸው መኝታ ለሽፋሽፍቶቻቸውም እንቅልፍ” ያልሰጡትን (መዝሙር 132፥4) እና “እየጸለያችሁ ሁልጊዜ ትጉ” (ሊቃስ 21፥36) የሚለውም ትእዛዝ የጠበቁትን ይሰበስባል… ነገር ግን ፃዲቅ ሰው ከሐዋሪያው ጋር በመሆን “ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ” (ገላትያ 6፥14) ብሎ መናገር የሚችል ሌላ ዓይነት መጨረሻ አውቃለሁ። ምክንያቱም ዓለም ለተሰቀለበት ሰው የዓለም መጨረሻ አስቀድሞ መጥቷል። ለአለማዊ ነገሮችም ለሞተ ሰው የጌታው ቀን ደርሷል፤ የሰው ልጅ ለኃጢአት ወይም ለአለም መኖር ወደተወ ወደ ጻድቅ ሰው ነፍስ ይመጣል” (ORIGEN)

ቁ40-41 “በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል ሌላው ይቀራል። ሁለት ሴቶች አብረው ይፈጫሉ፤ አንደኛዋ ትወሰዳለች ሌላይቱ ትቀራለች”፥ …

መለኮታዊ ጥሪ እና የሰው ልጅ ምላሽ በተለመዱት የሕይወት ክስተቶች መካከል (የእርሻ ሥራ፣ የባለሙያ ተግባር፣ የቤት ውስጥ ሥራዎች እና ሌሎችም) ይከናወናል። በዚህ ዕለታዊ መስክ ውስጥ ዘላለማዊ ደስታችን ወይም ዘላለማዊ ፍርድ ይወሰናል። እራሳችንን ለማዳን አስደናቂ ድርጊቶችን መፈጸም አያስፈልግም፤ በተለመደው ዕለታዊ ሥራ ውስጥ ለጌታችን ታማኝ መሆን በቂ ነው።

ቁ42-43 “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንደሚመጣ አታውቁምና ተግታችሁ ጠብቁ። ነገር ግን ይህን እወቁ፥ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ሰዓት ሌባ እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፣ ነቅቶ በጠበቀ ነበር”፥ …

“የቤት አባወራ የሰውን ነፍስ ይወክላል፤ ሌባ ዲያብሎስ ነው፤ ቤቱ አካል ነው፤ በሮች አፍና ጆሮዎች ሲሆኑ መስኮቶቹ ደግሞ ዓይኖች ናቸው። ሌባ የቤቱን ባለቤት ለመዝረፍ በበሮችና በመስኮቶች በኩል እንደሚገባ፣ ዲያቢሎስም የሰውን ነፍስ ይዞ ለመውሰድ በአፉ፣ በጆሮዎቹና በአይኖቹ በኩል መግባት ይችላል። ትምቢተ ኤርምያስ “ሞት በየመስኮታችን ገብቶአል” (እርምያስ 9፥21) የፃፈው ለዚህ ነው”። (INCOMPLETE WORK ON MATHEW)

ቁ44 “ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና”፥ …

እያንዳንዱ ቀን የህይወቱ መጨረሻ እንደሆነ፣ ክርስቲያን ነቅቶ መኖር አለበት።

አጭር ትምህርት

በሰብከተገና ጊዜ ይበልጥ መጸለይ፣ የተሻለ ጸሎት መጸለይ አለብን። ምን ማድረግ አለብን? አዲስ ነገር እንደሚከሰት እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል። አዲስ ነገር እንደሚከሰት ታምናለህን? የእግዚአብሔርን ክስተት እየጠበቅህ ነውን? በውስጥህ በእርግጠኝነት ስለሚከሰተው አዲስ ነገር የመጠባበቅ መንፈስ ከሌለህ፣ ወደ ሰብከተገና አልገባህም። አንዳንድ ሰው አውቶቡስ በየፈርማታ ላይ እንደሚጠበቅ ያለ እምነትና ፍቅር ክርስቶስን ይጠብቃል።

አዎን፣ ጸጋውን ከለመንክ እግዚአብሔር በህይወትህ ውስጥ አዲስ ነገር ያመጣል እንዲሁም ወደዚህ ሰብከተገና ያመጣል። ልክ እንደ ቤተልሔም ህፃን፣ ሊታይና ሊዳሰስ የሚችል አዲስ ነገር ነው። ይህ ሁሉ ካልሆነ፣ ሰብከተገና ምንድነው?

እግዚአብሔር ዓለምን ለማደስ ይመጣል። ዓለም በክፉ ትጠፋለች፣ ነገር ግን የዓለም መጥፋቱ በእግዚአብሔር ለሚያምኑ ሰዎች ድህንነት ትሆናለች። ነፃነታችን ቅርብ ነው! ዛሬ ከእግዚአብሔር ጋር ለመሆን ወደ ጸሎት እንመለስ!

“የተጀመረውን ነገር ያላወቀ እንዴት እንደሚጨርስ ግልፅ ሊሆንለት አይችልም” (AUGUSTINE De civitate Dei, VII, 8)

“ነፍስ ሆይ ፣ ክንፎችሽን አጣጥፊ፣ ከሩቅ ተመለሺ፣ ከሰማይ ወደ ታች ወደ ትንሹ ቤትሽ ውረጂ። አንቺ የስውር ሰማዕት፣ በስውር የሚኖረውን አምላክ የምትወጂ፣ የማይታየውን እግዚአብሔር የምትናፍቂ ነሽ! ያለ  እርምጃ መራመድ ይቻላልን? ባዶ አየር ውስጥ መግባት ይቻላል? ያለ ቃላት ለዘላለም በፍቅር መኖር ይቻላል?

እርምጃሽን ሰብስቢ፣ ልብሽን ጥሪ፣ እርምጃሽና ልብሽን ወደ ቤትሽ ሰብስቢያቸው። ምክንያቱም፣ ታያለሽ፣ በእርሻዎችሽ በኩል ተደስቼ እመጣለሁ፣ እረፍት በማያቋርጥ እልልታ በበልግ በኩል እቀድምሻለሁ። መላእክት መንገድ ላይ ናቸው፣ ትልልቅ ከዋክብት ወደዚህ ምድር እየተጓዙ ናቸው፥ የነርሱ ብርሀን በእያንዳንዱ ሕፃን ግንባር ይበራል” (Gertrud Von le Fort)

Leave a reply